ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የተፈራሙትን ስምምነት ተፈጻሚነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ በትብብር ለመስራት የተፈራረሙትን ስምምነት ተፈጻሚነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)  ከደቡብ አፍሪካ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ብሌድ ንዚማንዴ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ሁለቱ አገራት በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መስኮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል። 

አገራቱ እ.አ.አ በሴፕቴምበር ወር 2021 በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን በትብብር ለመስራት የተፈራረሙት ስምምንት አፈጻጸም በውይይቱ ላይ ተገምግሟል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በ10 አመት እቅዷ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን እንዲሁም ዲጂታላይዜሽን ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ በመሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪና በተለያዩ መስኮች ያላቸው ውጤታማ ግንኙነት የአፍሪካዊያንን ትብብር ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ አፍሪካ የሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ብሌድ ንዚማንዴ (ዶ/ር) ሀገራቸው በስፔስና አስትሮኖሚ፣ በምርምር፣በባዮ ኢኮኖሚ፣በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ)፣በናኖ ቴክኖሎጂ እና የሰው ኃይል ልማት ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማከፈልና የኢትዮጵያን ልምድም ለመቅስም ዝግጁ ናት ብለዋል።

አፍሪካውያን በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ አገር በቀል እውቀቶችን በመጠቀም በአጀንዳ 2063 የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ከሶስት ዓመት በፊት በተፈራረሙት ስምምነትበስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአስትሮኖሚ እንዲሁም በባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች ላይ በትብብር እየሰሩ ይገኛል።

ከውይይቱ ጎን ለጎን በባዮና ኢመርዲንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እየተሰሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች ጉብኝት ተደርጓል።

በውይይቱ ሁለቱ ሀገራት በዘርፉ የጋራ ስራዎችን ማከናወን የሚያስችል የጋራ ፈንድ ለማፈላለግና ለመመደብ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም