በክልሉ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን ለመተግበር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን ለመተግበር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
መቀሌ፤ ህዳር 18 / 2017 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ።
አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት የግል ባለሃብቶች በዘርፉ ላይ እንዲሰማሩ የሚጋብዝ በመሆኑ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።
የቢሮው ኃላፊ ኢያሱ አብረሃ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በትግራይ ክልልም የሚያሰራና ተቀባይነት ያለው ነው።
ቢሮው ፖሊሲና ስትራቴጂውን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ለመተግበር የሚያስችል የስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከወዲሁ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው የዘርፉ ፖሊሲ የግል ዘርፉን የማያሳትፍና የአርሶ አደሩን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር የማይፈታ እንደነበር ዶክተር ኢያሱ አውስተዋል።
አዲሱ ፖሊሲና ስትራቴጂ ግን ሰው ጉልበት ከመጠቀም ባለፈ ተጨማሪ የግብርናና ገጠር ልማት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የእርሻ ሜካናይዜሽንን የሚያስፋፋ እና የግል ዘርፉን ወደ ግብርና እንዲገባ የሚያበረታታ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑም ባለሃብቶች ወደ ክልሉ መጥተው በዘርፉ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ፖሊሲው በተለይ ለአርሶ አደሩ መሬቱን አስይዞ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር የማግኘት መብት እንደሰጠው ነው ኃላፊው ያመለከቱት።
"በእርሻ ዘርፍ የሰው ጉልበት የሚተካና ምርታማነትን የሚያሳድግ ቴክኖሎጂ ያስፈልጋል" ያሉት ዶክተር ኢያሱ፤ አዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ይህንኑ የሚተገብር እና ገበያ ተኮር ምርቶችን የሚያመርት አርሶ አደር የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የፖሊሲው እና ስትራቴጂው ቁልፍ ውጤት ቀጣይነት ያለው ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚለውን እይታ የሚያሰፋ እና የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተለይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሃገር ውስጥ መተካት የሚለው ስትራቴጂ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
የክላስተር፣ የመስኖ የሜካናዜሽን እና የሌማት ትሩፋት ኢኒሼዬቲቮችን በክልሉ ለመተግበር የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ኃላፊው አስረድተዋል።