ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ታግዘው የተሻለ ስራ እያከናወኑ ነው

አርባምንጭ ፤ህዳር 17/2017(ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ታግዘው የተሻለ ስራ እያከናወኑ መሆኑን የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በክልሉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ምልከታና ድጋፍ እያደረጉ ነው።


 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ፣ በክልሉ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ምቹ የሆነ ሰፊ ሀብት እንዳለ ገልጸዋል።

በተለይም አቮካዶ፣ ሞሪንጋና ሌሎች የግብርና ምርቶች በስፋት እየተመረቱ ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እየሆኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ታግዘው ያለውን የግብርና ሀብት በተሻለ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ንቅናቄው በወላይታ ሶዶ፣ በጌዴኦ ዲላ፣ በጋሞ ዞን አርባምንጭ እና በሌሎች ከተሞች የተለያዩ የመካከለኛና ዝቅተኛ ኢንዱስትሪዎች የግብርና ምርት በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከ2 ሺህ 500 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ጥላሁን አክለዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጃጋማ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።


 

ለአብነትም ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያት ሥራ ያቆሙ 771 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው ንቅናቄው የዘርፉን ተወዳዳሪነት እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ በየዓመቱ ከ236 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሆነ ገልጸው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በመልካም ደረጃ ላይ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪው ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም የላቀ ሚና እንዲወጣ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች የተዘጉና በሙሉ አቅም የማያመርቱ ኢንዱስትሪዎችን በማነቃቃት ወደ ሥራ ማስገባቱን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም