በዞኑ የዘመናዊ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የዘመናዊ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ
ወልዲያ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ):- በሰሜን ወሎ ዞን አርሶ አደሩን የዘመናዊ መስኖ አውታር ተጠቃሚ ለማድረግ ከ464 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ12 መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ደሳለ ባዬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የአርሶ አደሩን የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዙ የመስኖ ተቋማት እየተስፋፉ ነው።
ባለፉት ሦስት ዓመታትም ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት 85 ሺህ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጉ የመስኖ አውታሮችን በመገንባት 16 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ ማልማት መቻሉን ገልፀዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመትም የ12 መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን የዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
መስከረም 2017 ዓ/ም መጨረሻ ጀምሮ የሦስት አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝና የግንባታ አፈፃፀማቸውም ከ90 እስከ 95 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ኃላፊው አቶ ደሳለ አመልክተዋል።
በዚህ ሳምንት የቀሪዎቹ መስኖ ተቋማት ፕሮጀክቶችን በማስጀመር እስከ ሚያዝያ 2017 ዓ.ም የሁሉም ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ታሳቢ ተደርጎ እየተከናወነ እንደሆነም አብራርተዋል።
እነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች 1 ሺህ 825 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው ሲሆን፤ ከ4 ሺህ 700 በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አንደሚያደርጉም ገልፀዋል።
ለፕሮጀክቶቹ ግንባታም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች 464 ሚሊዮን 698 ሺህ ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በሃብሩ ወረዳ የቁጥር አራት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማይ አበበ በሰጡት አስተያየት፤ አካባቢያቸው ዝናብ አጠር በመሆኑ እስከዛሬ የሚፈልጉትንና በልፋታቸው ልክ ምርት እንደማያገኙ አስታውሰዋል።
አሁን በአካባቢያቸው እየተገነባ ያለው የመስኖ ካናል ግንባታ ሩብ ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚያስችላቸው ጠቁመው፤ ከታህሳስ 2017 ዓ.ም ጀምረው ወደ ልማት እንደሚገቡ ተናግረዋል።
"የበርካታ ዓመታት የመስኖ ልማት ጥያቄያችን ዘንድሮ መልስ አግኝቶ እየተገነባልን ነው" ያሉት ደግሞ በጉባላፍቶ ወረዳ የአላውሃ ማመጫ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በላይ ተሰማ ናቸው።
በቅርብ ርቀት የሚገኘውን ወንዝ ለመጥለፍ የአቅም ውስንነት ገጥሟቸው እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ግን እርሳቸውንና ሌሎች በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በመስኖ ለማልማት የሚቻለውን አቅም ሁሉ አሟጦ ለመጠቀም በሁሉም አካባቢዎች የመስኖ አውታር ግንባታዎች እየተከናወነ እንደሆነም ታውቋል።