የፈረንሳዩ ምግብ ማቀነባበሪያ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የፈረንሳዩ ምግብ ማቀነባበሪያ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ የፈረንሳዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ዴላሞት ኢንተርፕራይዝ በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የደረቅ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ከዴላሞት ኢንተርፕራይዝ መስራች ሰባስቲያን ዴላሞት ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የተፈጠረው የስንዴ ምርት አቅርቦት መስተጓጎል ተጽእኖ እንዳያሳርፍባት በመንግስት በተወሰደው ርምጃ ከውጪ ስንዴ ለማስገባት ይወጣ የነበረው ከ750 ሚሊየን ዶላር በላይ በሀገር ውስጥ መተካት መቻሏን ጠቅሰው፤ በስንዴ አምራችነት ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ስንዴ ምርት አቅርቦትን በበላይነት እየመራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ኩባንያው በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ፋብሪካውን ከተከለ ከታክስ እና ከታክስ ውጪ ያሉ ማበረታቻዎችን እንደሚያገኝ ጠቁመዋል።
የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ባለሞያዎች የኩባንያውን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።
የኮርፖሬሽኑ ኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እና ማርኬቲንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዘመን ጁነዲ ኩባንያው የሚያስፈልገውን ምርት በኮንትራት ፋርሚንግ ቀጥታ ከአርሶ አደሮች መውሰድ የሚችልበት አማራጭ እንዳለ ገልጸዋል።
ለዚህም በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገኘው የፈረንሳዩ ብቅል አምራች ኩባንያ ሱፍሌትን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኩባንያው በኢትዮጵያ ላሉ ቢራ ፋብሪካዎች የሚያስፈልገውን ገብስ 70 ሺ ከሚደርሱ አርሶ አደሮች በኮንትራት ፋርሚግን ስርዓት እንደሚገዛ ጠቁመዋል።
የፈረንሳዩ የምግብ ማቀነባበሪያ ዴላሞት ኢንተርፕራይዝ መስራች ሰባስቲያን ዴላሞት ኩባንያው ለሚያመርተው ምርት ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ እቃዎችን ከኢትዮጵያ ለመጠቀም እንደሚፈልግ ገልጸዋል።
ኩባንያው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለመስራት ላሰበው ጣፋጭና ደረቅ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በዋናነት ስንዴ፣ የቅባት እህሎች እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ለመጠቀም ማቀዱን ጠቁመዋል።
የኩባንያው ባለቤቶች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ኢትዮጵያ የስንዴ ምርቷን ለማሳደግ ከፍተኛ ስራ እያከናወነች ባለችበት ወቅት ነው ብለዋል የኩባንያው መስራች።
ኩባንያው ለምርት ሂደቱ እስከ 10 ሺ ካሬ ሜትር የለማ መሬት እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኩባንያው በዘርፉ ያካበተውን የቴክኒክ እውቀት ለኢትዮጵያ ባለሙያዎች በማስተላለፍ ለሀገራዊ ክህሎትና እውቀት መዳበር የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚፈልግ መግለጻቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።