ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራች ነው- ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከል ማዕከል /ሮክ/ ውጤታማ የምርመራ፣ የክስና መረጃ ልውውጥ ስርዓት ማስፈን የሚያስችል ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ፤ የምስራቅ አፍሪካ ኢንሼቲቭ /ሮክ/ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ የቀጣናዊ ወንጀል መከላከል ስራዎችን ለመደገፍ የተመሰረተ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ በቀጣናው ህገወጥ የሰወች ዝውውርን በመከላከልና በተጎጂዎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል አቅም መገንቢያ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም የጋራ ግቦችን በማስቀመጥና መረጃ በመለዋወጥ የወንጀለኞችን የግንኙነት መረብ ለመበጣጠስ ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በመከላከል ጠንካራ አቋም እንዳላት ጠቅሰው ተፈላጊ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በማዋልና አሳልፎ በመስጠት ለቀጣናው ሰላም የጎላ አበርክቶ እያደረገች መሆኑን አብራርተዋል።

የዛሬው መርሀ ግብርም የባለብዙ ወገን ግንኙነቶችን በማሳደግ የመረጃ መለዋወጫ ስልቶችን ማስፋፋት ያስችላል ነው ያሉት።

የቀጣናዊ ትብብር ማዕከል /ሮክ/ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሔርቬ ጃሜት፤ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በሀገራት መካከል ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም አገራት ቀጣናዊ ትብብራቸውን በማጠናከር የመረጃና ደህንነት አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ሮክ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል የፋይናንስ ውስንነት እንዳለበት አንስተው፤ የዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብርን ይሻል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም