ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን 170 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ

ደሴ ፤  ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በመኸሩ ወቅት ከለማው መሬት ውስጥ 170 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለምቶ የደረሰ  ሰብል ብክነትን በሚቀንስ መልኩ መሰብሰብ መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዞኑ የደረሰው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳትና ብክነትን መቀነስ በሚያስችል አግባብ በቅንጅት እየተሰበሰበ ነው፡፡ 


 

በዘንድሮው የመኸር ወቅት 432 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከለማው ሰብል ውስጥ 200 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው ስንዴ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ከለማው መሬት 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። 

አርሶ አደሩ ማሳውን በየቀኑ በመቃኘት ቀድሞ የደረሰውን ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ እንዲሰበሰብ የማድረግ ስራ በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ170 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ጤፍ፣ ስንዴ፤ ማሾ፣ ቦለቄ፣ ምስር፣ አተር፣ ገብስና ሌሎች ሰብሎችን መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

የሰብል ስብሰባው ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተው፤ በጥንቃቄ እየተከመረና እየተወቃ ወደ ጎተራ እንዲገባም የባለሙያ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰብል አሰባሰቡን ተግባር ለማሳለጥና የምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወደ ስራ እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ አምስት የመውቂያ ማሽኖች ተገዝተው ሰሞኑን ለወረዳዎች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ በቃሉ ወረዳ አርሶ አደር ሰይድ አብዱ በሰጡት አስተያየት፤ ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ጤፍ፣ ማሽላ፣ ማሾና ቦለቄ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳይበላሽ በጥንቃቄ መሰብሰብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ ጥንቃቄ ሰብሉን እየወቁ ወደ ቤታቸው እያስገቡ መሆናውን ተናግረዋል፡፡

በመኸር ወቅቱ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ማሾ፣ ጤፍና ስንዴ በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ምክር ታግዘው በጥንቃቄ እየሰበሰቡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በተሁለደሬ ወረዳ የ014 ቀበሌ  አርሶ አደር አደም የሱፍ ናቸው፡፡

ሰብሉን ብክነትን በሚቀንስ አግባብ አብዛኛውን መሰብሰብ መቻላቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም  ሁሉንም ሰብስበው ለማጠናቀቅ ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት በሰብል ከለማው መሬት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱም ከግብርና መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም