ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተገነቡ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት ለቀጣናው በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው- የአገራት የመከላከያና ደህንት ተቋማት ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሰላምና ደህንነት ተቋማት ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መሰረት የሚጥል የቴክኖሎጂ አቅም መገንባታቸውን የተለያዩ አገራት የመከላከያና ደህንት ተቋማት ሚኒስትሮች ገለጹ፡፡

የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፍረንስ የተለያዩ አገራት ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት እና የፎረንሲክ ምርመራና ምርምር የልህቀት ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ህዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል፡፡

የማዕከሉ መከፈት ወደ ውጭ ተልኮ ሲከናወን የነበረውን የዘረመል (ዲኤንኤ) ምርመራ በሀገር ውስጥ እንዲሆን ከማድረግም ባሻገር የጎረቤት አገራት ጭምር እንዲገለገሉበት ታስቦ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራና ምርምር ልህቀት ማዕከል ወደ ውጭ ተልኮ ሲከናወን የነበረውን የዘረመል (ዲኤንኤ) ምርመራ ከማስቀረቱም ባለፈ የጎረቤት ሀገራትም የሚያገለግል መሆኑን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

የላይቤሪያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ፍረንሲስ ሰኪያ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው አህጉራዊ የሰላም ኮንፍረንስ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፡፡

አፍሪካ 67 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ምድር መሆኗን ገልጸው፤ ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ፣ ትምህርትና ማህበራዊ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

የወጣቶችን ፍላጎት ማስተናገድ ሳይችሉ ሰላም መፍጠር እንደማይቻል ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን በትብብር መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ የመከላከያና ወታደራዊ ዘማቾች ሚኒስትር አንጌ ሙትሰጋ፤ ኢትዮጵያ ለሌሎች አፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆኑ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን ገንብታለች ብለዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ጠንካራ የጸጥታና ደህንነት ተቋማት እንዳሉ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ተቋማት የተቀናጁና በቴክኖሎጂ የዳበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ የሰላምና ደህንነት ተቋማት ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መሰረት የሚጥል የቴክኖሎጂ አቅም መገንባታቸውን አይተናል ብለዋል፡፡

የታንዛኒያ ፖሊስ ኮሚሽነር ሬናታ ምዚንጋ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ  የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል የላቀና ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የታንዛኒያ የፎረንሲክ ምርመራ ፖሊስ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ትምህርት የሚቀስሙበትን መንገድ እንፈጥራለን ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም