ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው -- የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ህገ ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው -- የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን
አክሱም ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል አክሱምና አካባቢው የሚታየውን ህገ- ወጥ የቅርስ ዝውውር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አሳሰበ።
በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የህገ-ወጥ ቅርስ ዝውውር መከላከል ቀንን ምክንያት በማድረግ በአክሱም ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፀሃይ እሸቴ እንዳሉት፣ የዓለም መገለጫ እና የታሪክ ምስክሮች የሆኑ ቅርሶችን ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ፣ ለትምህርትና ምርምር ሥራ እንዲውሉ ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል።
ለቅርሶች ህገ-ወጥ ዝውውር ዋነኛ ምክንያት "እጅግ ውድ የሆኑ ቅርሶች በአግባቡ አለመመዝገባቸውና የሚሰጠው ትኩረትም አነስተኛ መሆን ነው" ብለዋል።
ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውርን ለመከላከል የመንግስት፣ የባለድርሻ አካላትና ከቅርስ ጋር ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ማድረግ የሚገባቸው ጥንቃቄ ላይ በስፋት ምክክር እንደተደረገበት መሪ ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
በምክክሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል በአክሱም ከተማ በአስተርጓሚነት ሙያ የተሰማሩት አቶ ፍፁም በላይ፤ ''ቅርሶችን ጠብቄና ተንከባክቤ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባባር ለመስራት ዝግጁ ነኝ'' ብለዋል።
በከተማ በአስጎብኝነት ሙያ የተሰማሩ መምህር ብርሃነ ታደሰ በበኩላቸው፣ ኑሯችን የተመሰረተው ቱሪስቶችን በመቀበልና በከተማው ያሉ ቅርሶችን በማስጎብኘት ነው ይላሉ።
በመሆኑ ህገ-ወጥ የቅርስ ዝውውር ሂደት የሚሳተፉ አካላትን ለማጋለጥ ድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
እድሜ ጠገብ ቅርሶቻችን ቱሪስቶችን በሚስብ መልኩ በማልማት ልንጠቀምባቸው ይገባል ያሉት ደግሞ ቄስ ተስፋይ ገብረጻድቅ ናቸው።
ቅርሶችን ከህገ ወጥ ዝውውር ለመታደግ ምዕመናኑን ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በስልጠናው ላይ ከትግራይ ማዕከላዊ ዞን ከ18 ገጠር ወረዳዎች የተወጣጡ የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አስጎብኝዎች፣ የህግና የፀጥታ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።