አፍሪካውያንን ከድህነት ለማውጣትና የበለጸገች አህጉር ለመገንባት አካታችና ዘላቂ መሰረተ ልማት ወሳኝ ነው- ሙሳ ፋኪ ማሃመት - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያንን ከድህነት ለማውጣትና የበለጸገች አህጉር ለመገንባት አካታችና ዘላቂ መሰረተ ልማት ወሳኝ ነው- ሙሳ ፋኪ ማሃመት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካውያንን ከድህነት ለማውጣት፣ የምንመኛትን የበለጸገች አህጉር ለመገንባት አካታችና ዘላቂ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ይህን ያሉት ስምንተኛው የአፍሪካ መሠረተልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ሳምንት የመክፈቻ መርሐግብር በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደበት ወቅት ነው።
የአፍሪካ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የበለፀገችና አንድነቷ የጠበቀ አፍሪካን እውን በማድረግ የትርክት ለውጥ ለመፍጠር ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
አፍሪካ የኢኮኖሚ ሽግግርን ጨምሮ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።
አጀንዳ 2063 ዘላቂና ለተፅዕኖ የማይበገር አዲስ የመሰረተ ልማት ስርዓትን ይፈልጋል ያሉት ሊቀመንበሩ፤ የአፍሪካ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የህብረቱ ሜጋ ፕሮጀክት ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አፍሪካውያንን ከድህነት ለማላቀቅና የበለጸገች አህጉር እውን ለማድረግ ለዘላቂና አካታች የመሰረተ ልማት ግንባታ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ምሳሌ የሚሆን ድንበር ዘለል የመንገድና የኃይል መሰረተ ልማት እየገነባች ትገኛለች ብለዋል።
በአፍሪካ ወሳኝ አህጉራዊ መሠረተልማቶችን ለመገንባት በቂ የፋይናንስ አቅም ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የግል ዘርፍና የመንግስትን አጋርነት ማጠናከር ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የመሠረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር አማኒ አቡ ዘይድ (ዶ/ር)፤ የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ባለፉት ዓመታት አህጉራዊ ትስስርን የሚያጠናክር ምቹ ምህዳርን ፈጥሯል ብለዋል።
በፕሮግራሙ 30 ሀገራትን ያስተሳሰሩ የመንገድና የባቡር መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናርዶስ በቀለ፤ የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ትግበራ አፍሪካ በቁርጠኝነትና በአንድነት ህልሟን ማሳካት እንደምትችል ማሳያ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ እስከ 2040 ድረስ ለአካታች መሰረተ ልማት ግንባታ 360 ቢሊዮን ዶላር ቢያስፈልግም የተሰበሰበው 80 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በጨለማ ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያንን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን መሰረተ ልማት ለማሟላትና አፍሪካን የታዳሽ ኃይል ጋን ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በ2040 በአፍሪካ 80 በመቶው ህዝብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን የኃይል መሰረተ ልማት ማስተር ፕላን እየተተገበረ መሆኑን ያነሱት ስራ አስፈጻሚዋ በቀጣይ የአፍሪካውያንን ህይወት የሚቀይር መሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ፤ አፍሪካ ህዝቧን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሰረተ ልማት እየገነባች ቢሆንም አሁንም ከፍተኛ ክፍተት አለ ብለዋል።
ይህ የመሰረተ ልማት መጓደልም የአህጉሪቱ የምጣኔ ሃብት እድገት 2 በመቶ እና ምርታማነትን ደግሞ በ40 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በቂ መሰረተ ልማት አለመኖሩ ከአህጉሪቱ አጠቃላይ ንግድ ውስጥ በሀገራት መካከል ያለው ልውውጥ 15 በመቶ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግና ለዘላቂ የመሰረተ ልማት ግንባታ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ መሠረተልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (PIDA) ለድንበር ተሻጋሪ መንገዶች፣ ለኃይል መሠረተ ልማት፣ ለውሃና ኢንፎርማሽን ቴክኖሎጂ መሠረተልማቶች መስፋፋት በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የሚተገበር ተነሳሽነት ነው።