ኢትዮ ቴሌኮም የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ሲስተም አበለጸገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ሲስተም አበለጸገ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ሲስተም አበለጸገ።
ኢትዮ ቴሌኮም ያበለጸገውን ሲስተም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ያስተዋወቀ ሲሆን በሲስተሙ ዙሪያ ግብዓት አሰባስቧል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሲስተሙ የድረ ገጽ ዓይነት ፕላት ፎርም ሲሆን የኢትዮ ቴሌኮምን ክላውድ በመጠቀም የሚሰራ ነው፡፡
በውስጡም የምርት ዓይነቶችን፣ ግብይት እና ሎጂስቲክስን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ ሲስተሞችን ያካተተ ነው።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በሲስተሙ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሲስተሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ አገራዊ እንቅስቃሴ አካል ነው ብለዋል።
ሲስተሙ ገዥና ሻጭ የሚገናኙበት፣ ኩባንያዎች የንግድ ግንኙነት የሚፈጥሩበት እንዲሁም አምራቾች ግብዓት የሚያገኙበት መሆኑን አብራርተዋል።
ሲስተሙ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ምርቶች በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለገበያ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አንድ ምርት የት ይገኛል ከሚለው ጀምሮ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ ዲጀታል በሆነ መንገድ ሂደቱን ማስተዳደር የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
መሰል ቴክኖሎጂን መጠቀም ካልተቻለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ኢንዱስትሪዎች ዲጂታል አሰራሮችን በመተግበር ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ሲስተሙን ወደ ሥራ ለማስገባት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ መወሰዱን ጠቅሰው በዘርፉ የነበሩ ችግሮች ላይ ዳሰሳ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት መርኃ ግብር ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን መሰል ዲጂታል አሰራሮች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ አምራች ዘርፉን በዘመናዊ አሰራር መደገፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ቴክኖሎጂን መጠቀም በትንሽ ወጪ ብዙ ምርት ለማግኘት እንዲሁም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሲስተም መዘርጋት ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ የአምራች ኢንዱስትሪው ተሳትፎ ወሳኝ ነው ሲሉም አሳስበዋል።