በክልሉ የቤተሰብ እቅድ አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን ግንዛቤ በመፍጠር እንዲያግዙ ተጠየቀ

ባህር ዳር ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል የቤተሰብ ምጣኔ እቅድ አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን መረጃ ተደራሽ በማድረግ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እንዲያግዙ ተጠየቀ።  

"ጥራት ያለው የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን እኔም ሀላፊነት አለብኝ" በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ቀን በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተከብሯል።


 

በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ዳይሬክተር አቶ መልሰው ጫንያለው እንደገለጹት፤ የቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀ የተመጠነ ቤተሰብ እንዲኖር ማስቻል ነው።

በተጨማሪም በውርጃ ምክንያት በእናቶች ህይወትና ጤና ማጣት ላይ የሚከሰተውን ችግር ለመከላከል እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ቀደም ሲል እንደ ክልል ጥሩ ተሞክሮ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ የተዛነፈ የአመለካከትና አተገባበር ችግር እንደሚስተዋል አመልክተዋል።

በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ እቅድ አተገባበር እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ችግሩን በማሳየትና የቤተሰብ ምጣኔ እቅድ እንዲተገበር የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ጽንስና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር እዮብ ሙሀመድ በበኩላቸው፤ እንደ አገር ባለፉት ዓመታት በጠንካራ ቅንጅት በተከናወኑ ስራዎች ለውጥ ማምጣት መቻሉን ገልጸዋል።


 

ማህበሩ  ገቢን መሰረት ያደረገና ጤናው የተጠበቀ ዜጋ እንዲኖር ህብረተሰቡንና የጤና ባለሙያዎችን የማስልጠን ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

"የቤተሰብ ምጣኔ ዓለማው ያልታቀደ እርግዝናን መከላከል ነው" ያሉት ዶክተር እዮብ ፤ ይህም የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስና ደህንነቱ የተጠበቀ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል። 

ህብረተሰቡ በተፈጠረለት ግንዛቤ ልክ የቤተሰብ ምጣኔ እቅድ አጠቃቀሙ እንደሚጨምር ጠቅሰው፤ ለዚህም መገናኛ ብዙሃን በመረጃ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ በመፍጠር የአገልግሎቱን ተጠቃሚዎች መጠን ማሳደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ማህበሩ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ውጤታማ የሆነ የቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ እንዲኖር ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በአገር አቀፍ ጀረጃ ለ9ኛ እና በክልል ደረጃ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ዕቅድ ቀን መረሃ ግብር ላይ የጤና ዘርፉና  የሀይማኖት ተቋማት አመራር አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም