የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያስከትል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያስከትል እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያስከትል እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ተናገሩ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባው ለፌደራል መንግስት የ2017 በጀት አመት 582 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።
ተጨማሪ ረቂቅ በጀቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በጀቱ የሚውልባቸውን ዋና ዋና ዘርፎችና የሚሸፈንበትን አግባብ አስረድተዋል።
ለመደበኛ ወጪ 393 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪ 70 ቢሊዮን ብር እና ለወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ 119 ቢሊዮን ብር መያዙን ገልጸዋል።
ከተጨማሪ በጀቱ 185 ቢሊየን ብር ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ዕዳ ክፍያ ፣ 208 ቢሊየን ብር ለማህበራዊ ድጎማ ፣ 60 ቢሊየን ብር ለማህበራዊ ሴፍቲኒት ማስፋፊያ ፣ 10 ቢሊየን ብር ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስተካከያ እና 119 ቢሊየን ብር የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ለማድረግ እንደሚውል ተናግረዋል።
ከታክስ በሚገኝ ገቢ 281 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፣ ከውጭ አገር እርዳታ የበጀት ድጋፍ 123 ቢሊዮን ብርና ከውጭ አገር ብድር የበጀት ድጋፍ 177 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪው እንደሚሸፈን ጠቅሰዋል።
ከአለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(አይ ኤም ኤፍ) በቀጥታ የበጀት ድጋፍ 300 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መገኘቱ ተገልጿል።
የምክር ቤት አባላት ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ንረትን እንዳያስከትልና በህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጥር ታሳቢ የተደረጉ ሁኔታዎችን ጠይቀዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ ተጨማሪ በጀቱ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ታሳቢ በማድረግና የዋጋ ንረትን በማያስከትል መልኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሰረት ከብሔራዊ ባንክ የረዥም ጊዜ ብድርን በማስቀረት የዋጋ ንረትን ለመከላከል ተሰርቷል ነው ያሉት።
የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪ፣ እድገቱን ዘላቂ ለማድረግና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ለማስተካከል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ማሻሻያው በጥቂት ወራት የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያን ከመደበኛ ገበያው እንዲቀራረብ ማድረጉ፣ የዋጋ ንረት አለማስከተሉን ጠቅሰው በተረጋጋ ማህበራዊ ሁኔታ እየተተገበረ ይገኛል ነው ያሉት።
ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የኑሮ ጫና እንዳያስከትል የደሞዝ ጭማሪ እንዲሁም በነዳጅ፣ ማዳበሪያና ሌሎች ዘርፎች ላይ ድጎማ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚው የሚፈጥረው መደበኛ እንቅስቃሴና የተደረጉ የታክስ ማሻሻያ አሰራሮችና አዋጆች የሚሰበሰበውን ገቢ እንደሚጨምሩት ታሳቢ መደረጉንም ተናግረዋል።
እንደሚኒስትሩ ገለጻ ማሻሻያው ህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያስከትል ጥንቃቄ የተደረገ ሲሆን ለከተማና ገጠር ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ድጋፍ በማድረግ በዘላቂነት ከተረጅነት ማውጣት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ በሶስት ተቃውሞና አምስት ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተጨማሪ በጀቱን አጽድቋል።
ምክር ቤቱ በዛሬ መደበኛ ስብሰባው አቶ ሃጂ ኢብሳን የፌደራል ምክትል ዋና ኦዲተር እንዲሆኑ የቀረበለትን ሹመት አጽድቋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት እና የመድኃኒት ፈንድን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን በማጽደቅ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሒሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።