ኢትዮጵያና ኬንያ በወታደራዊ መስክ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኬንያ በወታደራዊ መስክ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ኬንያ በወታደራዊ መስክ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በኬንያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሐሪሪ የተመራ ወታደራዊ ልዑክ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላና ከኃይልና ከዋና መምሪያ ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያና ኬንያ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው ፤ ሀገራቱ ግንኙነቱን ለማጠናከር በወታደራዊ ትብብር መስክ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በልማት የተሳሰሩ መሆናቸውን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አልሸባብን በጋራ ከመከላከል ጀምሮ በፀጥታና ደህንነት በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጅት መጠናቀቁን ጠቁመዋል።
የኬንያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሐሪሪ በበኩላቸው በጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ ለተደረገላቸው የጉብኝት ግብዣ በማመስገን ኢትዮጵያና ኬንያ ለቀጣናው ደህንነት ወሳኝ ሀገሮች ናቸው ብለዋል።
ከዚህ አንፃር በርካታ ዓመታት ያስቆጠረውን ወታደራዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መደረሱን አመልክተዋል።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳና የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄነራል ይመር መኮንን ለወታደራዊ ልዑኩ እንደ ተቋም ያለውን የሰራዊት ዝግጁነት የስልጠና ተቋማትና ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ያላትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ መከላከያ መረጃ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያና የኬንያን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር እንዲሁም ቀጣናውን አስመልክቶ አሁናዊና ቀጣይ ሁኔታን ያመላከተ ገለፃ ቀርቧል።
የወታደራዊ ልዑክ ቡድኑ በተለያዩ ወታደራዊ ተቋማት ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።