የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ አወገዘ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ አወገዘ።
በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር እና በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና ሞት በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ በመግለጫቸው ሁሉም ኃይማኖቶች ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርን፣ መተዛዘንን፣ ይቅርታና እርቅን የሚያስተምሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በመላ ሃገሪቱ ፍቅርን በመስበክ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር መስራት እንደሚገባ አንስተው ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ግድያ፣ እገታና መፈናቀል እየተስተዋለ መሆኑን አንስተዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በቅርቡ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ በማውገዝ ለቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን ተመኝተዋል።
የግጭትና የሰላም እጦት ጉዳይ የኃይማኖት አባቶችን እያሳሰበ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በገለልተኝነት የትኛውንም አካል ለማቀራረብ፣ ለማደራደርና ለማስታረቅ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በግጭት ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይትና ድርድር ለመፍታት ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጪው ሕዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም በመቄዶኒያ አረጋውያን መርጃ ማሕበር ለሀገር ሰላም የሚደረግ የፀሎት ፕሮግራም እንደሚኖርም ጠቁመዋል።