መዲናዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ለአካባቢ ብክለት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መዲናዋን ውብና ፅዱ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ለአካባቢ ብክለት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ፅዱና ተወዳዳሪ ከተማ ለማድረግ ለሚሰራው ስራ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላት ለአካባቢ ብክለት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ ።
የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተቋማት ቅንጅታዊ ስራዎችን እቅድ አፈፃፀም በጋራ ገምግሟል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ እንዳሉት አዲስ አበባ ከተማን ከብክለት የጸዳች እንደስሟ ዉብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚሰራው ስራ የአንድ አካል ተግባር ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተቋማት ርብርብ የሚጠይቅ ነው።
ባለስልጣኑ ከበርካታ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ቅንጅታዊ አሰራሩ ተቋማት ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አስችሏል ነው ያሉት።
ከብክለት የፀዳችና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ከተማ ለመፍጠር በሚሰራው ስራ ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
እንደምክትል ስራ አስኪያጁ ገለፃ የአካባቢ ጥበቃ ስራ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ በመሆኑ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው።
ካሁን ቀደም ተቋማት በግላቸው ሲያከናውኗቸው የነበሩ ስራዎች ውጤታማ እንዳልነበሩ ገልፀዋል።
ባለስልጣኑ ይህንን በመመልከት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት በመፈራረም ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።
በዚህም ካሁን ቀደም ከነበረው የተሻለ ውጤታማ ስራ ማከናወን መቻሉን ነው የገለፁት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት እውን በሆኑት የአረንጓዴ አሻራ፣ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ላይም በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ቅንጅታዊ አሰራሩ የተቋማት የቁጥጥርና የመከታተል አቅም እንዲጨምር ማድረጉንም ነው የጠቀሱት።
ባለፋት ስድስት ወራት "ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ" በሚል የተከናወነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደጉ በመድረኩ ተነስቷል።