ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ልጆቻቸው በተደረገው እንክብካቤ የአብራክ ክፋያቸውን መታቃፋቸውን እናቶች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ልጆቻቸው በተደረገው እንክብካቤ የአብራክ ክፋያቸውን መታቃፋቸውን እናቶች ተናገሩ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ልጆቻቸው በተደረገው እንክብካቤ የአብራክ ክፋያቸውን መታቀፉቸውን እናቶች ተናገሩ፡፡
ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው የተወለዱ ጨቅላ ህፃናት አለም አቀፍ ቀን በክቡር ዶክተር አበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል በውይይት ተከብሯል።
በመላው አለም በአመቱ 15 ሚሊየን የሚጠጉና ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው የተወለዱ ህፃናት ጤናማ እንዲሆኑ ልዩ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
በውይይቱ ላይ ከመውለጃ ቀናቸው ቀድመው የወለዱ እናቶች የሆስፒታል ቆይታቸውንና አጠቃላይ ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
ከአምስት ወር በፊት ሶስት ልጆችን በአንዴ የተገላገሉት ወይዘሮ ጋዲሴ ከበደ መውለጃቸው ሲቃረብ ወደ ክቡር ዶክተር አበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል መግባታቸውን ይናገራሉ።
በሆስፒታሉ በነበራቸው የ 45 ቀን ቆይታ ሀኪሞች ያደርጉላቸው በነበረው ሁለንተናዊ እንክብካቤ ቆይታቸውን በሙሉ መተማመንና በተስፋ ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል።
በሆስፒታሉ ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው ለተወለዱ ልጆቻቸው የተደረገው እንክብካቤ ልጆቻቸውን ታቅፈው ወደ ቤታቸው እንደሚገቡ ተስፋን የሰነቁበት እንደነበር አይዘነጉትም።
አሁን ላይ አምስት ወር የሞላቸው ልጆቻቸው በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ በደስታ ስሜት ተሞልተው ተናግረዋል፡፡
ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው የሚወለዱ ጨቅላ ህፃናት አስፈላጊውን እንክብካቤ ካገኙ በተሟላ ጤንነት መኖር እንደሚችሉ ምስክር ነኝ ብለዋል።
በደም ግፊት የተነሳ እዚሁ ሆስፒታል ገብቼ ሶስት ወራት ቆይቻለሁ ያሉት ወይዘሮ ሊያ አብርሃ በበኩላቸው በጤና ባለሙያዎች በተደረገላቸው የህክምና ክትትል ከመወለጃ ቀኑ ቀድሞ የተወለደ ልጃቸውን ታቅፈው በሰላም ቤታቸው እንደገቡ ነው የተናገሩት።
በሆስፒታሉ በወር እስከ 1 ሺህ እናቶች የወሊድ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ዱረቲ ጀማል አስታውቀዋል።
ይህ እንዳለ ሆኑ አሁን ላይ የተገልጋይ እናቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
ሆስፒታሉ 60 አልጋ በሚይዘው የጨቅላ ህፃናት ህክምና ክፍል በወር ከ250 በላይ ለሆኑ ጨቅላ ህፃናት ህክምና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ያለጊዜያቸው ለተወለዱ ህፃናት ማሞቂያ ክፍልና የመተንፈሻ አጋዥ መሳሪያዎችን በማዘጋጀትና የተለያዩ ህክምናዎችን በመስጠት የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ህፃናትና አፍላ ወጣቶች መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ማርያማዊት አስፋው በበኩላቸው በኢትዮጵያ በየአመቱ 376 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው እንደሚወለዱ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናት መጠነ ሞትን በመቀነስ በኩል ስኬት ብታስመዘግብም የጨቅላ ህፃናት መጠነ ሞትን በሚፈለገው ልክ መቀነሰ አለመቻሉን ነው ያስረዱት።
ሚኒስቴሩ የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስና የጤና ተቋማት ጥራት ያለውና ደረጃውን የጠበቀ የጨቅላ ህፃናት ጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ከአጋር አካላት በመተባበር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም 214 ሆስፒታሎች ፅኑ የጨቅላ ህፃናት ህክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡
በተጨማሪም ከ2 ሺህ 800 በላይ ጤና ጣቢያዎች የጨቅላ ህፃናት እንክብካቤ ኮርነር እንዲኖራቸው መደረጉን ተናግረዋል።
80 ሆስፒታሎች የደረጃ ሶስት ፅኑ የጨቅላ ህፃናት ህክምና አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት አግባብ ማደራጀት መቻሉን ገልፀው የጨቅላ ህፃናትን ህክምና ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
አለም አቀፍ ከመወለጃ ቀናቸው ቀድመው የተወለዱ ጨቅላ ህፃናት ቀን በአለም ለ14ኛ በኢትዮጵያ ለ11ኛ ጊዜ "ተደራሽና ጥራት ያለው እንክብካቤ በሁሉም ቦታ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው ተከብሮ የዋለው።