በደብረ ማርቆስ ከተማ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን እና ልማትን ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

ደብረ ማርቆስ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦  በደብረ ማርቆስ ከተማ ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን እና ልማትን ለማሳለጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የህብረተሰቡ አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ። 

''ሁሉም ለሰላም፤ ሰላም ለሁሉም'' በሚል መሪ ሃሳብ ከከተማው ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ እንዳሉት፤ በከተማው ሰላምን በዘላቂነት ማስፈን የሚቻለው ሁሉም የሰላም ባለቤት ሆኖ በቁርጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሲሰራ ነው።

 የዘላቂ ሰላም መስፈን ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመፍታትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

እንደ ከተማ አስተዳደር በተቀናጀ መንገድ በተሰራ ስራ አሁን ላይ ሰላምን በማስፈን የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

መንግስት አሁንም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እና ልማት እንዲፋጠን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ይህንኑ በማገዝ ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ የፖለቲካ እና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ መልካሙ ሽባባው በበኩላቸው፤ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ በተጓዳኝ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲቀጥሉ ህብረተሰቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ ማበርከት እንዳለበት አመልክተዋል።


 

አሁን የተገኘው ሰላም ሊመጣ የቻለው ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ባደረገው ተሳትፎ መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም በሚኖርበት አካባቢ ሰላሙን መጠበቅ፣ በተሳሳተ መንገድ የሚቀሳቀሱ አካላትን መምከር እና ትክክለኛ መስመር እንዲይዙ ማገዝ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አበበ መኮንን፤ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ንጹህ አያሌው ናቸው።

በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላትና ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተወጣጡ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም