ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያሏት ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የጋራ እሴቶችን አስጠብቆ መቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ

ሆሳዕና ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦  ኢትዮጵያ ያሏት ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የጋራ እሴቶችን አስጠብቆ መቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ ፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ሀገራዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ክላስተር በሚገኙ አመራሮችና ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል፡፡ 

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ  ባዩሽ ተስፋዬ (ዶ/ር)እንዳሉት ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል ታሪክና እሴት መገለጫዎች ያሏት ሀገር ናት፡፡ 


 

ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም ተደማሪ እሴት ለማምጣት የጋራ የሆኑ እሴቶቻችንን አስጠብቆ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡ 

በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሁሉንም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተቀናጅቶ መጓዝን እንደሚጠይቅ ገልፀዋል፡፡ 

ለዚህም ስኬት የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቁንጮ የሆነውን የፌዴራሊዝም ስርዓትን አስጠብቆ ማስቀጠል ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድም ተናግረዋል፡፡ 

ለዘላቂ ሰላም መጠበቅና ለሀገራዊ ልማት መረጋገጥ የፌዴራሊዝም ስርዓቱን በተገቢው መንገድ እንዲተገበር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል። 


 

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ደህንነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ተመስገን ቶማስ በበኩላቸው መንግሥት የፌዴራሊዝም ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ የዴሞክራሲ ምህዳርን በማስፋት የዜጎችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

''ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታን ለመፍጠር በህብረ-ብሔራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ አካሄድን መከተል ለሁለንተናዊ እድገታችን በጎ ተፅዕኖን ይፈጥራል'' ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ሀገራዊ ግንባታን ማጠናከርን በማለም በየዓመቱ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ማክበሯ ለዚህ አንዱ ማሳያ ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡ 

ከነጠላ ትርክት በመውጣት የጋራ ትርክቶችን በማጎልበት በቅንጅት መጓዝ ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚጥል በመሆኑ በዚህ ላይ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ 

ከክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን አቶ ተስፋዬ አሰፋ እንደገለፁት ህብረ ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት መጓዝ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ 

ነባር ችግሮችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የወል ትርክቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ጠቃሚ መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡ 

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በክላስተሩ በሚገኙ ሴክተሮች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም