ቀጥታ፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ 582 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት የ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ 582 ቢሊዮን ብር በጀት አጽድቋል።

ምክር ቤቱ እያካሄደ ባለው 6ኛ መደበኛ ስብሰባው የቀረበለትን ተጨማሪ ረቂቅ በጀት መርምሮ አጽድቋል።

ረቂቅ በጀቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) የበጀቱን አስፈላጊነትና የሚውልባቸውን ዋና ዋና ዘርፎች ዘርዝረዋል።


 

ለመደበኛ ወጪ 393 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪ 70 ቢሊዮን ብርና ለወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ 119 ቢሊዮን ብር መሆኑን በማብራሪያቸው ገልጸዋል።

ተጨማሪ በጀቱ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ዕዳ ክፍያ 185 ቢሊዮን ብር፣ ለማኅበራዊ ድጎማ 208 ቢሊዮን ብር፣ ለማኅበራዊ ሴፍቲኔት ማስፋፊያ 60 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስተካከያ 10 ቢሊዮን ብርና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ለማድረግ 119 ቢሊዮን ብር እንደሚውል ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ በሦስት ተቃውሞና አምስት ታቅቦ በአብላጫ ድምጽ ተጨማሪ በጀቱን አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም