ኢትዮጵያ በሱዳን ያለው ግጭት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሱዳን ያለው ግጭት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት - ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሱዳን ያለው ግጭት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሊ የሱፍ አሕመድ አል-ሻሪፍን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች በተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮች እና በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሱዳን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጻ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በግጭቱ ምክንያት ከሀገራቸው ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ የሱዳን ዜጎች ላደረገችው አቀባበልና ድጋፍ በሱዳን ሕዝብ ስም አመስግናል።
ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሱዳን ያላትን አጋርነት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
የሱዳን ወንድሞቻችንን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደ ጎረቤት ሀገር ያለብን ግዴታ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ በሱዳን ያለው ግጭት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባከበረ መልኩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድጋፏን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ጨምሮ ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ፍላጎታቸው በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን የቀጥታ ምክክርና ቀጣይነት ያለው ግንኙነት መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች በውይይታቸው ሀገራቱ መደበኛ የፖለቲካ ምክክሮችን በማድረግ ትብብራቸውን እንዲጠናከርና ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስራቸው እንዲጎለበት በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።