ቀጥታ፡

የአፍሪካን መፃኢ ጊዜ የተሻለ ለማድረግ ዘላቂና አካታች መሠረተ ልማት ግንባታን ማጎልበት ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካን መፃኢ ጊዜ የተሻለ ለማድረግ ዘላቂና አካታች መሠረተ ልማት ግንባታን ማጎልበት ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የገነባቻቸው የመንገድና የኃይል መሠረተ ልማቶች ቀጣናዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ ለአህጉራዊ ግቦች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ይህን ያሉት ስምንተኛው የአፍሪካ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ሳምንት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተከፈተበት ወቅት ነው።

የአፍሪካ መሠረተ ልማት ፕሮግራም ችግሮችን የሚቋቋምና አካታች መሠረተ ልማትን በመዘርጋት አህጉራዊ አቅሞቻችንን ለመጠቀም ወሳኝ ሚና አለው  ብለዋል።

ይህም አካታች ዕድገትና የጋራ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና አለው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ፕሮግራሙ የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት ዋነኛ መሣሪያ እንደሆነም ተናግረዋል።

ድንበር ተሻጋሪ መሠረተ ልማት ለቀጣናዊ ትስስርና የጋራ ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ጠቅሰዋል።


 

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የምዕራፍ አንድና ሁለት ትግበራ በተጣጣመ መልኩ ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ማከናወኗን ተናግረዋል።

ለመንገድ፣ ለባቡር መሥመርና ለታዳሸ ኃይል የተሰጠው ትኩረት የሀገሪቱን መሠረተ ልማት እያሻሻለ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መሥመር ቀጣናዊ ትስስርን ከማጎልበቱም ባለፈ የትራንስፖርት ወጪን በመቀነስ የንግድ ልውውጥን እያፋጠነ ነው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለበርካታ ሀገራት ዜጎች የታዳሽ ኃይል የሚያቀርብና አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቷን ለዘላቂ ልማት ማዋል እንዳለባት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።

ሀገሪቱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት ለቀጣናዊ ትስስር እያደረገች የምትገኘው ጉልህ ሚና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

በአፍሪካ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም እስካሁን በተደረገው ጥረት ሀገራትን ከሚያገናኙ የፍጥነት አውራ መንገዶች እስከ ኃይል ኮሪደሮች በርካታ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሰሜን-ደቡብ እና በማዕከላዊ አፍሪካ ኮሪደሮች በርካታ ሀገራትን የሚያስተሳስሩ ፕሮጀክቶች እውን መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ኮሪደሮቹ አህጉራዊ እንቅስቃሴን በማሻሻል፣ የንግድ ልውውጥን በማሳደግ እና ለቀጣናዊ ትብብር አዳዲስ እድሎችን በመፍጠር ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ሆኖም የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት እያደረሱ በመሆኑ ዘላቂና የማይበገር መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።

ለመሠረተ ልማት የሚሆን በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ለመፍጠርም የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን ማጠናከር፣ ቀጣናዊ ኢንቨስትመንትን ማበረታታትና ችግር ፈቺ መፍትሔ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም መንግሥታትና ባለድርሻ አካላት ለአፍሪካ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም መሳካት ቁርጠኝነታቸውን እንዲያድሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (PIDA) ለድንበር ተሻጋሪ መንገዶች፣ ለኃይል መሠረተ ልማት፣ ለውሃና ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች መስፋፋት በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የሚተገበር ተነሳሽነት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም