ቀጥታ፡

በግብርና መካናይዜሽን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ መጨመር ችለናል - የአርሲ ዞን አርሶ አደሮች 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦መንግሥት በዘረጋው የግብርና መካናይዜሽን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ መጨመር መቻላቸውን የአርሲ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። 

መንግስት እየተከተለ ያለው የመካናይዜሽን ግብርና የአርሶ አደሩን ድካም ከመቀነስ ባሻገር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ብክነትን ለማስቀረት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአርሲ ዞን ሔጦሳ ወረዳ በኮምባይነር የሚሰበሰብ የስንዴ ምርትን ጎብኝተዋል።

በአርሲ ዞን በትራክተር ማረስን ጨምሮ ምርትን በኮምባይነር መሰብሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለመደ መምጣቱን አርሶ አደሮች ይናገራሉ። 

በዚህ ዓመት በዞኑ 450 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ምርት መሸፈኑና 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ በጉብኝቱ ላይ ተመላክቷል።

በሔጦሳ ወረዳ ምርታቸውን በኮምባይነር ሲሰበስቡ ያገኘናቸው አርሶ አደር ሃጂቱኔ ሮባ መሬታቸውን በትራክተር አርሰው በኮምባይነር ማጨዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ምርታማነታቸውን በእጥፍ ማሳደጋቸውን ጠቁመዋል፡፡


 

አርሶ አደር በሽር ወይሶ በበኩላቸው የመካናይዜሽን መስፋፋት ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የምርት ብክነትን ለመከላከል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። 

ቆጥበው በገዙት ኮምባይነር የራሳቸውን ምርት ማጨድን ጨምሮ የአካባቢያቸውን አርሶ አደሮች ምርት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደር ጀማል አማኖ በበኩላቸው መካናይዜሽንን በስፋት መጠቀማቸው ምርታማነታቸው በእጥፍ እንዲጨምር ማስቻሉን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሮቹ ከዚህ ቀደም ከሄክታር ያገኙት የነበረውን ከ20 ኩንታል የማይበልጥ ምርት ዛሬ ላይ በዘመናዊ አስተራረስ በመታገዝ ከአንድ ሄክታር ከ40 እስከ 60 ኩንታል ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል። 


 

የሔጦሳ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወል ዋፎ በበኩላቸው፤ በወረዳው 42 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ምርት መሸፈኑንና ከዚህ ውስጥ 36 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በክላስተር የታረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በወረዳው መካናይዜሽንን ለማስፋፋት ትልቅ ትኩረት መስጠቱን የገለጹት አስተዳዳሪው በርካታ አርሶ አደሮች ትራክተር እና ኮምባይነር መግዛታቸውን ተናግረዋል።

የመካናይዜሽን መስፋፋትም ምርትን በእጥፍ ለመጨመር ማገዙን ጠቁመው በወረዳው ከአንድ ሄክታር ከ40 እስከ 80 ኩንታል ምርት እንደሚገኝም ጠቁመዋል።


 

የአርሲ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሂርጳ ዳባ በዚሁ ወቅት፤ በአርሲ ዞን 450 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑንና በምርት ዘመኑ 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

የመካናይዜሽን መስፋፋት አርሶ አደሩን ወደ ባለሃብትነት እየቀየረው መሆኑን ጠቁመው 1 ሺህ 446 አርሶ አደሮች በዚህ ዓመት ወደ ኢንቨስትመንት እንደሚሸጋገሩ ነው ያስረዱት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም