ኢትዮጵያ እና ሕንድ ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ሕንድ ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ሕንድ ያላቸውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ትብብር የጋራ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍስሐ ሻውል የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሕንድ ፕሬዝዳንት ድሮፓዲ ሙርሙ አቅርበዋል።
አምባሳደር ፍስሐ ሻውል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን የሰላምታ መልዕክት ለፕሬዝዳንት ድሮፓዲ አድርሰዋል።
አምባሳደሩ እና ፕሬዝዳንቷ የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ትብበር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሰው ሀብት ልማት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በሎጅስቲክስ እና በትራንስፖርት ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ማጎልበት እንደሚገባም አንስተዋል።
ሀገራቱ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ለጋራ ፈተናዎቻቸው መፍትሔ ለማበጀት እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በኒው ዴልሂ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።