ቀጥታ፡

ከ403 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ባደረገው ክትትል በአንድ ሳምንት ብቻ ከ403 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን አስታወቀ፡፡

ከህዳር 6 እስከ 12/2017 በተደረገ ክትትል 386 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 16 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ 403 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውንም ገልጿል፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የግንባታ እቃዎች፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደገኛ እጾች፣ መድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ የውጭ ሀገር ገንዘቦች እና የጦር መሳሪያዎች እንደሚገኙበት አስታውቋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ  የተያዙ መሆናቸውንም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 26 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እና 20 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም