ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ የስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል። 

ወላይታ ድቻ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 10 ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በያሬድ ገመቹ የሚመራው ወላይታ ድቻ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።

ቡድኑ በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 10 ግቦችን አስተናግዷል። ወላይታ ድቻ በ13 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። 

በጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ጎሎችን አስተናግዷል። በውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ በሰባት ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የስምንተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በስሑል ሽሬ እና ባህር ዳር ከተማ መካከል ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

ስሑል በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። በጌታቸው ዳዊት የሚሰለጥነው ስሑል ሽሬ በሰባት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች በሶስቱ ድል  ሲቀናው በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። 

ቡድኑ በሰባቱ ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል። 

በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ በ10 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች  ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ቡናን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የሊጉ መሪ መቻል አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም