አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊዮኖች የሚያልቁበት የረሀብ ታሪክ አይደለም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 17/2017(ኢዜአ)፦አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት በአርአያነት የሚጠቀስ ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊዮኖች የሚያልቁበት የረሀብ ታሪክ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ተቀንቅኖ ድጋፍ የተሰበሰበበት Do they know its Christmas?  መዚቃ አሁን ላይ ዳግም መለቀቁ የኢትዮጵያን አሁናዊ የልማት ጉዞ ያላገናዘበ ገጽታን የሚያበላሽ ተረክ መሆኑንም ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ በ1977 የተከሰተው ድርቅ ያስከተለውን ሰፊ ጉዳት ተከትሎ አይርላንዳዊው ሙዚቀኛ ቦብ ጊልዶፍና መሰል እውቅ ሙዚቀኞች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል Do they know its Christmas? የሚለውን ሙዚቃ አቀንቅነው ከፍተኛ ድጋፍ አሰባስበዋል። 

 የዚህ የሙዚቃ 40ኛ ዓመት ዘንድሮ የተከበረ ሲሆን በወቅቱ የተሰራው ሙዚቃ ዳግም ተለቋል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሙዚቃ 40ኛ ዓመት ሲዘከር ሙዚቃው ዳግም እንዲለቀቅ መደረጉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መናገራቸውን "ዘ ታይምስ" የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሙዚቃው ላይ እንደተገለጸችው ሳይሆን በፈጣን እድገት ውስጥ  የምትገኝ መሆኗን ገልጸዋል።

ሙዘቀኞቹ በወቅቱ የሰሩት ሥራ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ሙዚቃው  ዛሬ ላይ ከጊዜው ጋር አብሮ አለመሄዱ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጠቁመዋል። 

ሙዚቃው የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ያቃለለና ሰዋዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ተረክ የያዘ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ ያለ የኢኮኖሚ ባለቤት፣ ታሪካዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎቿ ከሚጎበኙ ሥፍራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን እንዲሁም በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች ያለች አገር ሆና ብትታወቅ ይጠቅም ነበር ብለዋል።  

ሙዚቃው አሁን እኛ ለምንፈልገው ኢንቨስትመንት የሚጠቅም አይደለም፤ ድርቅ አሁን ላይ እኛን አንደ አህጉርም እንደ አገርም አይገልጸንም ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በረሃብ ልትታወቅ አትችልም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንፆት ሰጥተዋል። 

በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍና በሌሎች መስኮች እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ዳግም ረሃብ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውንም ጠቅሰል። 

ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ችላለች፤ ሌሎች ምርቶችንም በአገር ውስጥ ምርት መተካት አቅም ፈጥራለች ብለዋል። 

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአፍሪካ ሊጠቀስ የሚችል የግብርና ዘርፍ አብዮት እያካሄደች መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ሙዚቃ የተለያዩ ወቀሳ እየደረሰበት መሆኑን  "ዘ ታይምስ" ጋዜጣ ዘግቧል።

ሙዚቃው አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 እንደ አዲስ ሲሰራ እውቁ እንግሊዛዊው ኢድ ሺራን በሙዚቃው ከተሳተፉ አርቲስቶች መካከል አንዱ ነበር። 

ይሁንና አሁን ላይ ሙዚቃው የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ እንደማይገልጽ በሚሰነዘርበት ወቀሳ በወቅቱ በሙዚቃው ተሳትፎ ባላደርኩ እስከማለት መደርሱም በዘገባው ተጠቅሷል።   

በመድረክ ስሙ ፉስ ኦ ዲ ጂ የተሰኘው የጋና ሙዚቀኛ፤ ሙዚቃው የተጠቀማቸው የግጥም ስንኞች አፍሪካን በተመለከተ አሉታዊ መልዕክት እንዳላቸው ጠቅሷል። 

ይህም የአፍሪካን ልማት፣ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት አድገት ያቀጭጨዋል ብሏል።

ይህንን መልዕክቱን በማኅበራዊ ሚዲያ የጋራ ሲሆን እውቁ ሙዚቀኛ ኢድ ሺራንም ይህንን መልዕክት ተጋርቶታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም