ቀጥታ፡

የጀጎል ግንብ ከዓለም አቀፍ ቅርስነት የመሰረዝ የስጋት መዝገብ ውስጥ ወጥቶ ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ መሆን ችሏል - አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ የጀጎል ግንብ ከዓለም አቀፍ ቅርስነት የመሰረዝ የስጋት መዝገብ ውስጥ ወጥቶ ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ መሆን መቻሉን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

አቶ ኦርዲን በድሪ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው የጀጎል ግንብ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የአለም ቅርስ ስፍራነት ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል አንዱ መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

የዚህ አይነት የቅርስ ከተሞች በዓለም ቀደምት የስልጣኔ ከተሞች ከሚጠቀሱ የአውሮፓና እስያ አህጉራት ውስን አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው ብለዋል።

ከለውጡ ዓመታት በፊት የጀጎል አጥሮች በህገ ወጥ ግንባታ ተወረው፣ ከአጥሩ ውስጥም የቅርስ ይዘቱን ያልጠበቁ ግንባታዎች ተበራክተው፣ የቆሻሻ መጣያና መፀዳጃ ከመምሰላቸው የተነሳ ቅርሱን ከዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ስፍራነት የሚያሰርዝ ስጋት ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህ ደግሞ ለሀረር ከተማ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለዘመኑ ትውልድ የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ነበር ብለዋል።


 

ይሁን እንጂ ይህ ስጋት በተጨባጭ ችግር ሆኖ ሳይመጣ በመሪዎች የሀሳብ ልእልና በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ሁኔታውን በመቀልበስ የጀጎል ግንብ እና አካባቢው በቂ ጥበቃና እንክብካቤ የማግኘት እድል ማግኘቱን ገልጸዋል።

በዚህም የጀጎል ግንብ ከዓለም አቀፍ ቅርስነት የመሰረዝ የስጋት መዝገብ ወጥቶ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ እየሆነ መምጣቱን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።

ይህ የሆነው በብልጽግና ዘመን ነው ያሉት አቶ ኦርዲን የብልጽግና የወል ትርክት፣ የአብሮነት፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት እሳቤዎች የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት እየፈጠሩ ነው ብለዋል።

ስራውን ህዝብ የተቀበለውና የተሳተፈበት በመሆኑ ውጤቱ ያማረ እንዲሆን አድርጎታል ነው ያሉት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመሩት የቱሪስት መዳረሻዎች ልማት ኢንሼቲቭ የጀጎል ቅርስን መልሶ ለማልማት ከፍተኛ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ በቅርስ አካባቢዎች ምቹ የእግረኛ መንገዶች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የመንገድ መብራቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተሟልተው ምቹ የኑሮ አካባቢ እንዲሆን ትልቅ እገዛ ማድጉንም አመልክተዋል።

ጀጎል ግንብ ዙሪያው 3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከፍታው ደግሞ በአማካይ 5 ሜትር መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም