ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረው መነቃቃት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እድል ፈጥሯል-ሚኒስቴሩ

ሀዋሳ ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረው መነቃቃት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እድል መፍጠሩን  የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት በንቅናቄው የተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ በሃዋሳ ተካሄዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረው መነቃቃት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እድል ፈጥሯል፡፡

ከንቅናቄው በኋላ 741 የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች የተከፈቱ ሲሆን አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ዘርፉን መቀላቀላቸውንና የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ማነቆዎች በመፍታት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ላለው "የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" ውጤት ቀጣይነት ክልሎችን ያሳተፈ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የሲዳማ ክልልም ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት አቋቁሞ እያከናወነ ያለው ተግባር በዘርፉ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ተቀናጅቶ ለመፍታት የሚያስችልና ተሞክሮ የሚወሰድበት በመሆኑ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያጋጥመውን የፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት፣ የገበያና ሌሎች መሰረታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ ስራ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ንቅናቄው የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ተኪ ምርቶችን በማምረት  ከ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪን ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቆዎች በቅንጅት ለመፍታት የሚያስችል እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

ንቅናቄውን ተከትሎ በክልሉ የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት መቋቋሙን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተሰራው ስራም የተዘጉ ኢንደስትሪዎችን ወደ ስራ በማስገባት የማምረት አቅምን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡ 

በክልሉ የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክና የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክን ጨምሮ 1 ሺህ 302 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በስራ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ናቸው፡፡

ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኋላ ባለድርሻ አካላት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰጡት ትኩረት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው የክልሉ መንግስትም ለመሸጫና ማምረቻ ማዕከላት ግንባታ ከፍተኛ በጀት መመደቡን ጠቅሰዋል፡፡

በመድረኩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተከናወኑ ሃገር አቀፍና ክልላዊ ሰነዶች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የመንግስት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም