መንግሥት ሁሉን አቀፍ የከተሞች የአረንጓዴ ትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ሁሉን አቀፍ የከተሞች የአረንጓዴ ትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ መንግሥት ሁሉን አቀፍ የከተሞች የአረንጓዴ ትራንስፖርት ሥርዓት ለመዘርጋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።
በነገው ዕለት በይፋ የሚከፈተው የአፍሪካ መሰረተ ልማት መርኃ ግብር ሣምንት አካል የሆኑ የውይይት መድረኮች በአፍሪካ ኅብረት ተካሂዷል።
"ለችግሮች የማይበገሩና አካታች መሰረተ ልማት ማስፋፋት ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት" በሚል መሪ ኃሳብ ከተደረጉ መድረኮች የኢትዮጵያ የግሪን ሞቢሊቲ ተሞክሮ ላይ የመከረ የፖናል ውይይት ይገኝበታል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሐሠን በዚሁ ጊዜ፤ የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ፖሊሲ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልፀዋል።
ለታዳሽ ኃይል ተሽከርካሪዎች በተሰጠው ትኩረት የከተማ ትራንስፖርት ሥርዓት ለዚህ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሰረት ልማቶች ግንባታዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ እንዲሁም የመንገድ ደኅንነት ሀገራዊ ስትራቴጂ መቅረጿን ጠቁመው፤ የመንገድ፣ የባቡርና የአየር ትራንስፖርት በታዳሽ ኅይል የማስተሳሰር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም ለግሪን ሞቢሊቲ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየች መሆኑን ነው ያነሱት።
የነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን ለመቀነስና በኤሌክትሪክ ለመተካት በታዳሽ ኃይል የተሰማሩ ኩባንያዎች ከፍተኛ ማበረታቻ መደረጉን አስታውሰዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በመገጣጠም ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች እየተበራከቱ መሆኑን ገልፀው፤ በቀጣይም የተሽከርካሪ ባትሪ በሀገር ውስጥ ለማምረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
ሌላው የመንግሥት ትኩረት የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፉን ማጠናከር እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
የግሉ ዘርፍ በሕዝብ የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሰማራ በተሰራው ሥራም አሁን ላይ በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገር ውስጥ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይ አስር ዓመታት በታዳሽ ሃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለማስፋት እየተሰራ ነውም ብለዋል።
በዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክሪስ ኮስት፤ የከተሞች ግሪን ሞቢሊቲን በተመለከተ የኢትዮጵያን ተሞክሮ አድንቀዋል።
መንግሥታት ተደራሸና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት ሥራዎች ጥራታቸውና ደኅንነታቸው የተጠበቀ ተደራሽ ትራንስፖርት ሥርዓት እየገነባች ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በከተማ መሰረተ ልማት ጅምሮች ጥራት ያላቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆኑ ገልፀው፤ የከተማ ስትራቴጂ ቀርፃ ወደ ተግባር መግባቷ በአርዓያነት የሚወሰድ እንደሆነም ነው ያነሱት።
የእግረኛ፣ የሳይክልና ተሽከርካሪዎች ጎዳናዎች በምሳሌነት የሚወሰዱ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ አሁንም ግን የህዝብ ትራንስፖርት ነጻ መንገዶች ጉዳይ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አንስተዋል።