የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን የማምረት አቅም 40 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን የማምረት አቅም 40 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት አመት የሀገር ውስጥ የመድኃኒት አምራቾችን የማምረት አቅም 40 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት በናይጄሪያ ሌጎስ በተካሄደው የ2024 አለም አቀፍ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ውድድር በምርጥ ኬዝ አቅራቢነት ተሸላሚ ሆኗል።
ይህንን አስመልክቶ በተዘጋጀ መድረክ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ እንዳሉት ሚኒስቴሩ መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲን እየተከተለ ይገኛል፡፡
ፖሊሲውን ተፈጻሚ ለማድረግ የመድኃኒት አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ የመድኃኒትና ህክምና ግብዓቶችን በጥራትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር መንግስት ድጎማ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም በጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር የሀገር ውስጥ አምራቾች ከአቅማቸው 25 በመቶ ያህሉን ብቻ ሲጠቀሙ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።
አሁን ላይ በተሰጠው ትኩረት የሀገር ውስጥ መድሃኒት አምራቾች አቅም 36 በመቶ መድረሱንና በተያዘው አመት ወደ 40 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚኒስቴሩን የመድኃኒት ግዢ የሚፈፅምና የሚያሰራጭ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይሀን ተከትሎ አሁን ላይ በተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የ2024 አለም አቀፍ የጤና አቅርቦት ሰንሰለት ውድድር ተሸላሚ መሆኑ እያከናወነ ያለው የለውጥ ስራ ውጤታማ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብድልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው የተገኘው ውጤት ተቋሙ የጀመረው ለውጥ ስኬታማ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ በመግለጽ በቀጣይም የያዘውን ራዕይ ማሳካት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በማዘመን የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።