የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ማገዝና መደገፍ የቀጣናውን ሰላም የማጽናት ስራ ነው - አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ማገዝና መደገፍ የቀጣናውን ሰላም የማጽናት ስራ ነው - አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ማገዝና መደገፍ የቀጣናውን ሰላም የማጽናት ስራ መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለጹ።
የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፈረንስ "የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ፤ በአፍሪካ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቷን ሰላም ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች ስለመሆኑ አንስተው በጥረቷ ልክ እገዛና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካሳየው ቁርጠኝነት ባሻገር በሽግግር ፍትህ ዘላቂ ፍትህና ሰላምን ለማረጋገጥ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ ወደ ተግባር መግባቱንም አድንቀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረትም የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ገቢራዊ እንዲሆን ከአንድ ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ መድረጉን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም ለምታደርገው ጥረት የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ውስብስብ ፈተናዎች የተባበረ ጥረትን የሚጠይቁ ናቸው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ማገዝና መደገፍ የቀጣናውን ሰላም የማጽናት ስራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት ሃላፊና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፤ ኮንፈረንሱ በውቧ አዲስ አበባ መዘጋጀቱ የተለየ የደስታ ስሜት ፈጥሮልኛል ብለዋል።
የሰላም ኮንፈረንሱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ አገራትና ለአህጉሪቷ ጭምር ወሳኝ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
የዓለምን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የአፍሪካን ሰላም መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህ ደግሞ በጋራ ተባብሮ መስራት ይገባል ብለዋል።
የሰላም ጉዳይ የሁሉንም የጋራ ጥረትና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል ብለዋል።