በሴቶች ላይ የሚደርስን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል የተጀመሩ ቅንጅታዊ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ድሬዳዋ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን አስቀድሞ የመከላከል እና በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃን ተግባራዊ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አስታወቁ፤
አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በአገር ደረጃ በድሬደዋ መከበር ጀምሯል። 

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ከማስከተሉ ባለፈ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን እየፈጠረ ይገኛል። 

ችግሩን አስቀድሞ የመከላከል እና በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል። 

ህገ መንግስቱን እንዲሁም አለም አቀፍ የሴቶችና የህፃናት መብቶችን ለማስከበር አዳዲስ አሠራሮች ተዘርግተው የሚወሰዱ ህጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልፀዋል። 


 

''ጥፋት የሚያደርሱ ሰዎችን በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በማጠናከር አስተማሪና ወሳኝ ቅጣት እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው'' ብለዋል። 

ችግሩ የደረሰባቸው ህፃናትና ሴቶች ሁለገብ የህክምና፣ የህግ እና ሌሎች የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችና የህፃናት ችሎት በማቋቋም  ቀጣይ ህይወታቸው የተሳካ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። 

በተለይ ከአለም ባንክ እና ከሌሎች አለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለጥቃት የተጋለጡትን ሴቶች በኢኮኖሚና በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው እንዲጎለብት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል። 

እነዚህን ጅምር ስራዎች ማጠናከርና ችግሩን መከላከል ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ዜጎች በተለይም የወንዶችን የተቀናጀ ርብርብና ድጋፍ ይጠይቃል ብለዋል። 

በዛሬው ዕለት በድሬደዋ መከበር የጀመረውና እስከ ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም በሚዘልቀው የፆታ ጥቃት አለም አቀፍ ቀን የተጀመሩ ተግባራትን በህዝባዊ ንቅናቄ ለማጀብ መደላድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። 

በአከባበሩ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን በበኩላቸው የሴቶችን እና ህፃናትን ሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ መብቶች እንዲከበሩ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በአስተዳደሩ በሁሉም መስክ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ በትኩረት መሰራታቸው መሠረታዊ ለውጦች እንዲመዘገቡ ቢያስችልም  አሁንም በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ሙሉ በሙሉ የማስቆም ስራ የሁሉም ዜጋ  ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

በድሬዳዋ አስተዳደር በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱትን ፆታዊ ጥቃቶች ለመከላከል ከፍትህ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ በመሆኑ በአሁን ወቅት የተሻለ ለውጥ እየተመዘገበ ነው ያሉት ደግሞ የድሬደዋ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሁክሚያ መሐመድ ናቸው። 


 

ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናትን ስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ህመሞች ለማዳን፣ በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ቅጣት ለመውሰድ የሚያስችል የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የሴቶችና ህፃናት ማገገሚያ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው። 

እነዚህን ጅምር ስራዎች ለማጠናከር በድሬዳዋ የተካሄደው አለም አቀፍ የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን የተሻለ ንቅናቄ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል። 

በበዓሉ ላይ የተገኙት የአለም አቀፍ አጋር አካላት ተወካዮች በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የፀረ ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

"የሴቷ ጥቃት የኔም ነው፤ ዝም አልልም" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በድሬደዋ መከበር በጀመረው አለም አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀን ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዘሓራ ሁመድ፣ የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የዘርፉ አመራሮች፣ የአለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም