በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማጠናከር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተስፋፋ ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማጠናከር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተስፋፋ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

በነገው ዕለት በይፋ የሚከፈተው የአፍሪካ መሰረተ ልማት መርኃ ግብር ሣምንት አካል የሆኑ የውይይት መድረኮች በአፍሪካ ኅብረት እየተካሄዱ ነው።

"ለችግሮች የማይበገሩ አካታች መሰረተ ልማት ማስፋፋት ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት" በሚል መሪ ኃሳብ ከተደረጉ መድረኮች የኢትዮጵያ የግሪን ሞቢሊቲ ተሞክሮ ላይ የመከረ የፓናል ውይይት ይገኝበታል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በረኦ ሀሠን በዚሁ ጊዜ፥ የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ፖሊሲ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልፀዋል።

በታዳሽ ኃይል ተሽከርካሪዎች ላይ በተሰጠው ትኩረትም የከተማ ትራንስፖርት ሥርዓት ለዚህ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ መሰረት ልማቶች ግንባታዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ እንዲሁም የመንገድ ደኅንነት አገራዊ ስትራቴጂ መቅረጿንም አንስተዋል።

የነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎችን ለመቀነስና በኤሌክትሪክ ለመተካት በተሰጡ ትኩረትም ባለፉት ዓመታት በታዳሽ ኃይል ለተሰማሩ ኩባንያዎች ከፍተኛ ማበረታቻ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ለአብነትም ባለፉት ዓመታት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በመገጣጠም የተሰማሩ ኩባንያዎች እየተበራከቱ መሆኑን ገልፀዋል።

ይህም ለግሪን ሞቢሊቲ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል።

የመንገድ፣የባቡርና የአየር ትራንስፖርት ማስተሳሰር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የግሉ ዘርፍ በሕዝብ የታዳሽ ኃይል ትራንስፖርት ዘርፍ እንዲሰማራ በተሰራው ሥራም አሁን ላይ በርካታ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በአገር ውስጥ እንደሚንቀሳቁሱ ገልፀዋል።

በዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክሪስ ኮስት፤ በከተሞች ግሪን ሞቢሊቲ በተመለከተ የኢትዮጵያ ተሞክሮ አድንቀዋል።

መንግሥታት ተደራሸና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሕዝብ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር ልማት ሥራዎች ጥራታቸውና ደኅንነታቸው በተጠበቀ ተደራሽ ትራንስፖርት ሥርዓት እየተገነባች ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከተማ መሰረተ ልማት ጅምሮች ጥራት ያላቸውና ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሆኑ ገልፀው፥ የከተማ ስትራቴጂ ቀርፃ ወደ ተግባር መግባቷ በአርዓያነት የሚወሰድ እንደሆነም ነው ያነሱት።

የእግረኛ፣የሳይክልና ተሽከርካሪዎች ጎዳናዎች ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞችም በምሳሌነት የሚወሰዱ እንደሆኑ ገልፀዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም