በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረውን መነቃቃት ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረውን መነቃቃት ለማስቀጠል በትኩረት ይሰራል
ሀዋሳ ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የፈጠረውን መነቃቃት ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ገለጹ።
የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አፈጻጸምና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በሀዋሳ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃትን ፈጥሯል።
በክልሉ በንቅናቄው የተፈጠረውን መነቃቃት በማጠናከር ውጤታማነቱን የበለጠ ለማረጋገጥ በተቀናጀ መንገድ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አቶ በየነ አክለውም በሲዳማ ክልልም ንቅናቄውን ውጤታማ ለማድረግ የኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት በማቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ንቅናቄው የአምራች ኢንደስትሪውን ዘርፍ ማነቆዎች በመፍታት፣ ድህነትን ለመቀነስና ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ለማግኘት የሚያስችል እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
መድረኩ የተሰናዳው የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠልና በተግዳሮቶች ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።