ቀጥታ፡

የቻይና ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው- ያንግ ይሃንግ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ይሃንግ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) ከአምባሳደሩ የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ የቻይና ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና እንዲጨምር ማድረግ ላይ ያተኮረ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የአዳማ ሁናን ኢንዱስትሪ ፓርክን የማስፋፊያ ግንባታ ለማስጀመር አዲስ አበባ ከሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ጋር በትብብር በሚሰሩ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሁለተኛ ምዕራፍ የሆነው የአዳማ ሁናን ፕሮጀክት ግንባታ የሚያስፈልገው 125 ሄክታር መሬት ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና ቻይናን የኢንቨስትመንት ትብብር ያደነቁት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ የሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁኔታዎች የማይለወጥ ወዳጅነት ላይ መድረሱ የወዳጅነታቸው ማሳያ ነው ብለዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት በኢንቨስትመንት መስኩም ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክቷል።

የቻይና ባለሀብቶች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጣና የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝ ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።

መንግስት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በተለይም በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ያደረገው ማሻሻያ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት መፍጠሩን ተናግረዋል።

የቻይና ባለሀብቶች ይህንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ በፓርኮቹ መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱና ለዚህም ኤምባሲው ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮርፖሬሽኑ ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር ጥረት እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች አማካሪ ያንግ ይሃንግ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኤምባሲው ከኮርፖሬሽኑ ጋር በኢንቨስትመንት ፤ በሰው ኃይል ልማት እና በልምድ ልውውጥ ያሉትን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የሁለቱ ወገኖች ትብብር በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ለሚሰሩ የቻይና ባለሀብቶች ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለመፍጠር እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

የቻይና ባለሀብቶች ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ፓርኮች ውስጥ መዋለ ንዋያቸውን ስራ ላይ ለማዋል ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሀገራቱን ዘላቂ ወዳጅነት ይበልጥ የሚያጠናከር መሆኑን አማካሪው መግለጻቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም