ኮፕ 29 ለኢትዮጵያና አፍሪካ የካርቦን ሽያጭን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ስምምነቶች የተገኙበት ሆኖ ተጠናቋል - የፕላንና ልማት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ የካርቦን ሽያጭን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥ ተስፋ ሰጪ ስምምነቶች በመፈራረም መጠናቀቁን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከሕዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ጉባዔ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

በጉባዔው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ቡድን ተሳትፎ አድርጓል።

የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አንቀፅ 6.2 እንዲሁም 6.4 መሰረት የካርቦን ሽያጭ ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ይህም ለኢትዮጵያና ለቀረው የአፍሪካ ክፍል በጎ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ስምምነት ጥላ ስር ኢትዮጵያ አስቀድማ የዘላቂ አረንጓዴ ልማት ትብብር መመስረትና አማራጭ ገቢ ማስገኛ ዕድሎቿን ማሳየቷን ገልጿል።

አረንጓዴ አሻራን ለማጠናከር ፣ የታዳሽ ኃይል ልማትና አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም የግብርና ዘርፍን ለማትጋት የሚያግዝ አቅምን የሚያልቅ እንደሚሆንም ታምኖበታል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ምሳሌ በሆነችበት የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በሀገራት መካከል ያለው ትብብር እንዲጠናከር በር እንደሚከፍት ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

ለዚህም ኢትዮጵያና አፍሪካ የጀመሯቸውን ጥረቶች በማጠናከር ቀሪ የቤት ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው ተመላክቷል።

በተጨማሪም በኮፕ 29 ጉባዔ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋሚያ የሚውል የ300 ቢሊዮን ዶላር የፋይናንስ አቅርቦት ስምምነትም ፀድቋል።

በጉባዔው ላይ 200 አገራት የሚጠጉ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል።

30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) እ.አ.አ በ2025 በብራዚል ቤሌም ከተማ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም