ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው-አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ

አዲስ አበባ፤ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለጹ።

የአፍሪካ አህጉራዊ የሰላም ኮንፈረንስ "የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በዚሁ ጊዜ፥ በአፍሪካ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቷን ሰላም ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ካሳየው ቁርጠኝነት ባሻገር በሽግግር ፍትህ አማካኝነት ዘላቂ ፍትህና ሰላምን ለማረጋገጥ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ ወደ ተግባር መግባቱንም አድንቀዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም