የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮችና ባለስልጣናት አህጉር አቀፍ የሰላም ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮችና ባለስልጣናት አህጉር አቀፍ የሰላም ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ የተለያዩ አገራት ሚኒስትሮች እና ባለስልጣናት የሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው አህጉር አቀፍ የሰላም ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
አህጉራዊ የሰላም ጉባዔው ዛሬ እና ነገ በአዲስ አበባ "የበለፀገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ ይከናወናል።
የደቡብ አፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሞትሸክጋ ማትሴ እና የልዑካን ቡድናቸው በጉባዔው ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) እና ሌሎች የሚኒስቴሩ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የሩዋንዳ ፣የቡሩንዲ ፣የላይቤሪያ ፣ የደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ የኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ዚምባቡዌ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች እና የስራ ኃላፊዎችበጉባዔው ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።
በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሃይማኖት ተቋማት አመራሮች፣ የአፍሪካ ወጣቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በጉባዔው ላይ ተሳታፊ ናቸው።
ጉባዔው የኢትዮጵያን የሰላም ግንባታ ሥራዎች ልምድ በማካፈል፣ በአፍሪካ ሀገራት መረጋጋት እና እድገት ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ ያሉትን የሰላም ችግሮች በመፍታት አህጉራዊ ሰላምና ብልፅግና እንዲረጋገጥ ለማድረግ መዘጋጀቱን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።