ቀጥታ፡

አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው በመላው አፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል ለመቻል የመጀመሪያውን ወርቅ አስገኘች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 16/2017(ኢዜአ)፦ አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው በሁለተኛው መላው አፍሪካ የጦር ኃይሎች የስፖርት ፌስቲቫል ለመቻል የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

በናይጄሪያ አቡጃ እየተካሄደ ያለው የስፖርት ፌስቲቫል ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል።

የመቻል ስፖርት ክለብ ኢትዮጵያን ወክሎ በአትሌቲክስ ውድድር ተሳታፊ ሆኗል።

በሴቶች የ5000 ሜትር ፍጻሜ አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አገኝታለች።

ሀምሳ አለቃ አያልፍም ዳኛቸው ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።


 

በሌሎች የውድድር ዘርፎች በርዝመት ዝላይ ሴቶች ምክትል አስር አለቃ በፀሎት አለማየሁና በዲስከስ ውርወራ ሴቶች አስር አለቃ ዙርጋ ኡስማን የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።

በውድድሩ ላይ በናይጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ለገሰ ገረመውና ሌሎች ዲፕሎማቶችና ሰራተኞች አትሌቶቹን አበረታተዋል።

በተመሳሳይ በ400 ሜትር ወንዶችና ሴቶች ማጣሪያ የተሳተፉት የመቻል አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ለፍፃሜ አልፈዋል።

የውድድሩ መርሃ ግብር ዛሬ ቀጥሎ ሲውል በወንዶች የርዝመት ዝላይ ፣ የጦር ውርወራና 400 ሜትር በወንዶችና ሴቶች እንዲሁም በወንዶች የ5000 ሜትር ፍፃሜ ውድድር ይካሄዳል።

መቻል በፌስቲቫሉ እስከ አሁን 1 ወርቅ እና 4 ብር በድምሩ 5 ሜዳሊያዎችን ማግኘቱን ከአገር መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በስፖርት ፌስቲቫሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ25 የአፍሪካ አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 184 ስፖርተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

ፌስቲቫሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በኬንያ አስተናጋጅነት ከተካሄደ በኋላ ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በድጋሚ መካሄድ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም