ያለፉት የለውጥ አመታት በርካታ ድሎችን ያስመዘገብንበት ነበር - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ)፦ ያለፉት የለውጥ አመታት በርካታ ድሎችን ያስመዘገብንበትና ተቃራኒ ኹነቶችንም ያስተናገድንበት ጊዜ ነበር ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ እንኳን ለብልፅግና ፓርቲ ምስረታ 5ኛ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ያለፉት የለውጥ አመታት በርካታ ድሎችን ያስመዘገብንበትና ተቃራኒ ኹነቶችንም ያስተናገድንበት ጊዜ ነበር ሲሉም ተናግረዋል።


 

ከመከፋፈል እና አግላይ የፖለቲካ እሳቤ ወጥተን አካታች፣ ሚዛናዊ እና ህብረ ብሄራዊ አንድነት የሚያፀና ሃገራዊ ፓርቲ በመመስረት ለኢትዮጵያ ብልጽግና ራዕይ ሰንቀን መትጋት የጀመርንበት አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

የለውጡ መንገድ አልጋ ባልጋ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለዘመናት ቀስፈው ከያዟት ጐታች አስተሳሰቦች እና ተግባራት ለማላቀቅ ከፍተኛ ትግል እና ውጣ ውረድ በፅናት ማለፍን የሚጠይቅ ነበር ሲሉም አክለዋል፡፡

ለማልማት ስንተጋ ለማጥፋት ከሚታገሉ ጋር፣ ለመገንባት ስንሯሯጥ ለማፍረስ ከሚጥሩ አካላትጋር ተፋልመናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው፡፡

እውነት ከውሸት ዘመን ጋር፣ ፅኑ እምነት ከጥርጣሬ እና ክህደት ጋር፣ መልካምነት ደግሞ ከክፋት ጋር የተፋለሙበት እና የታገሉበት ምእራፍን በማለፍ እውነት ይዘን፣ በጎነት እየተገበርን በፅናት እያሸነፍን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቁበትን አመታት አሳልፈናል ብለዋል፡፡

በአስቸጋሪ የጉዞ መንገድ የድል ፍሬዎች ውስጥ የሚጠቀሱ አንኳር ስኬቶች እያስመዘገብን ቃልን በተግባር በመፈፀም የፓርቲያችንን አላማ አሳይተናል ነው ያሉት።

ለመጪው ትውልድ የምናወርሰው እዳን ሳይሆን የበለፀገች እና የለማች ሀገር እና ከተማን እንደሚሆን ፅኑ እምነት አለን ሲሉም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብልፅግና መረጋገጥ አይቀሬነት በመገንዘብ በውጣ ውረዱ ጉዞ አብራችሁን የቆማችሁ፣ ስንተጋ ከእኛ ጋር የተጋችሁ፣ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ጥሪ ስናቀርብ በጐ ምላሽ የሰጣችሁን ነዋሪዎቻችንን በሙሉ በራሴ እና በፓርቲያችን ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም