የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ ሃኪም ትዕዛዝና ያለ አግባብ ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ ሃኪም ትዕዛዝና ያለ አግባብ ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባ አሳሰበ

ጅግጅጋ፤ ህዳር 15/2017 (ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ ሃኪም ትዕዛዝና ያለ አግባብ መጠቀም እንደሌለበት የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ አሳሰበ።
ዓለም አቀፍ የፀረ-ተህዋሲያን የመቋቋም ግንዛቤ መፍጠሪያ ሳምንት "እናስተምር፣ ጥብቅና ቁም፣ አሁን ተግብር” በሚል መሪ ሀሳብ በጅግጅጋ እየተከበረ ነው።
የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ አያንሌ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡ ያለ ሃኪም ትዕዛዝና ያለ አግባብ ጸረ ተህዋሲያን መድሀኒቶችን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚገባው አሳስበዋል ።
በህክምና ባለሙያ የታዘዘን መድሀኒት ብቻ በአግባቡ በመውሰድ በህመም ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን ችግር ማስቀረት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ቢሮው በአስር ሆስፒታሎች ኮሚቴ በማቋቋም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም በተጨማሪ ሰባት ሆስፒታሎች እንደሚቋቋም አመልክተዋል።
የሶማሌ ክልል የመድኃኒትና የምግብ ቁጥጥር ኤጀንሲ ኃላፊ አብዱላሂ መሀሙድ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመት ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን መጠቀም በመቻሉ በተላላፊ በሽታዎች የሚታመሙና የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር እንዲቀንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ይሁንና ህብረተሰቡ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ በዘፈቀደ መድሀኒቶችን በመውሰዱ ምክንያት ተዋህሲያኑ መድኃኒቶችን እንዲላመዱ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል ።
የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሼህ ሀሰን የበሬ ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል ተወካይ አብዲፈታህ ሙሀመድ (ዶ/ር)፤ “በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት በተሰጣቸው ህሙማን የህክምና መዝገቦች ላይ በተደረገ ግምገማ የፀረ-ተዋህሲያን መድኃኒቶች በሽታ የማጥፋትና የመፈወስ አቅማቸው እየቀነሰ መምጣቱ ተረጋግጧል “ ብለዋል ።
ተዋህሲያን መድኃኒቶችን የመቋቋም አቅም እንዲያዳብሩ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች አንዱና ዋናው ሰዎች ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒቶችን ያለ በቂ ምክንያትና ያለ አግባብ ስለሚጠቀሙ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ሳንባ ነቀርሳ ያሉ ተላላፊ በሽታዎች፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች፣ አጣዳፊ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች፣ ወባ፣ ተቅማጥና ሌሎችንም ለማከም አስቸጋሪ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮች፣ የክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።