የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወቅታዊ መግለጫ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወቅታዊ መግለጫ

የአማራ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ጽንፈኛ ኃይሎች በፈጠሩት ቀውስ የሰላም እጦት ገጥሞት የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን፣ በሕዝብ ስም እየማለ እታገልለታለሁ የሚለውን የአማራ ሕዝብ ለከፋ ጉዳት እና አሰቃቂ ችግሮች እየዳረገው ይገኛል፡፡
ጽንፈኛው ቡድን የሰዎች እና የምርት እንቅስቃሴ በክልሉ ውስጥ እንዳይኖር መሰናክል ፈጥሯል፤ ሰው እያገተ የድኻ ገንዘብ ዘርፏል፤ ሕፃናትን በማገት የቤተሰብ ጥሪት ከማሟጠጥ ጀምሮ ያገታቸውን ሕፃናት በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፤ አካባቢያቸው ሰላም እንዲሆን የጠየቁ የሀገር ሽማግሌዎችን አግቶ ገንዘባቸውን ከመዝረፍ በተጨማሪ በእንብርክክ አስኪዶ ገድሏቸዋል፤ አዳጊ ሕፃናትን ከትምህርት ገበታቸው እንዲነጠሉ አድርጓል፤ የሞያ ሥነ ምግባራቸውን እና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በትምህርት ገበታ ላይ የተገኙ መምህራንን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏቸዋል፤ በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ቦንብ በማፈንዳት በተማሪዎች ላይ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል፡፡
ከዚህም በላይ የሆኑ፣ የሰሚን ጆሮ ጭው የሚያደርጉ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈጽሟል።
ይህ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀስ ጽንፈኛ ኃይል፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን እና የሕዝብ አብሮነትን የማይቀበል ኋላ ቀር ኃይል ነው። ይልቁኑም መቃቃርን የሚፈጥር፤ የኅብረተሰቡን ዕሴት በመሸርሸር እና አሰቃቂ ጥፋቶችን በመፈጸም የተጠመደ አረመኔያዊ ቡድን ነው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ሽብርተኛው የሸኔ ቡድንም እታገልለታለሁ የሚለውን የኦሮሞ ሕዝብ እጅግ መራር እና አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ግድያ፤ እገታ፤ ዝርፊያ፤ አፈና እየፈጸመበት ይገኛል፡፡ ሁለቱም ጽንፈኛ ኃይሎች ለአንድ አሰቃቂ ዓላማ ሁለት ቦታ የተሰለፉ ዕኩይ ቡድኖች ናቸው። እየፈጸሙት የሚገኙት እኩይ ተግባር በጦር ሜዳ የደረሰባቸውን ኪሳራ ለማስቀየሻ የሚፈጽሙት ነው። መቃብራቸው የሚቆፈረው በሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ በመሆኑ፣ ሕዝብን እርስ በርስ ማጋጨት እና ንጹሐንን መጨፍጨፍ የትግል ስልታቸው ነው።
እነዚህ መቃብራቸው የተማሰ፣ ልጣቸው የተራሰ ጽንፈኛ እና ሽብርተኛ ቡድኖች፤ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደራ ወረዳ ያደረሱትን ዘግናኝ እና አሰቃቂ ድርጊት የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ በጽኑ ያወግዛሉ፡፡ ይህ ወንጀል ሰው የሆነ ፍጡር የማይፈጽመው የአውሬነት ተግባር ነው።
እነዚህ በጣዕረ ሞት ላይ የሚገኙ ጽንፈኛ ኃይሎች፣ ለዘመናት ማንም በማይበጥሰው የወንድማማች እና እኅትማማች ገመድ የተሣሠሩትን የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ለመነጣጠል እና ወደ ግጭት ለማስገባት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ነገር ግን ሰላም ወዳዱ እና አርቆ አሳቢው ሕዝባችን ነገሮችን በጥንቃቄ እና በአስተውሎት በማየት፣ ድርጊታቸውን እና ዓላማቸውን ቀድሞ በመረዳት፣ የጽንፈኞችን እና የሤረኞችን እኩይ እና አጸያፊ ተግባር በንቃት እየመከተ ይገኛል፡፡
የአማራ ሕዝብና የአማራ ክልል መንግሥት ከኦሮሞ ሕዝብና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን እነዚህ ዘግናኝ ተግባር የፈጸሙ ጽንፈኛ እና አሸባሪ ቡድኖች ለሕግ ቀርበው አስፈላጊውን ቅጣት እንዲያገኙ አበክረን እየሠራን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከውጭና ከውስጥ ጠላቶቻችን ጋር በጋራ የሚሠሩ፣ እንዲሁም እርስ በርሳቸው የሚናበቡ ጽንፈኛ ኃይሎች፤ በንጹሐን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ በመፈጸም በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚፈጽሙትን እኩይ ተግባር በአስተማማኝ ሁኔታ በመቀልበስ ብርቱ ክንዳችንን እያሳረፍንባቸው እንገኛለን። ወደፊትም ይህን ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡
መላው የክልላችን ሕዝብና ሌሎች ወንድም እና እኅት ኢትዮጵያውያን የሕግ የበላይነት እንዲከበር ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ የበኩላችሁን እንድትወጡ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላፋለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ኅዳር 15/ 2017 ዓ.ም
ባሕርዳር