ለኢትዮጵያ ዘላቂ የሰላም ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ዘላቂ የሰላም ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለምታደርገው ጥረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮች ገለጹ።
የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ያለው ስራ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በማጽናት ለዘላቂ ሰላም የሚደረገውን ጥረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአህጉራዊና ዓለማ አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት በመቀሌ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ የማቋቋም ስልጠና የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል።
በዝግጅቱ የተገኙት የአፍሪካ ሕብረት ተወካይ ሜጀር ጄኔራል ራዲና ስቴፈን፤ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት ሰላምን ለማጽናት የሚደረገው ጥረት በጥሩ ሁኔታ እየተጓዘ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት በተለያዩ ጊዚያት የተካሔዱ ስትራቴጂክ የአፈፃጸም የምክክር መድረኮች ላይ የፕሪቶሪያው ስምምነት የሰላም ሂደቱን ለማጽናት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን እንደተመላከተ ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ፈንድ፣ የአሜሪካ መንግስት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የመንግስታቱ ድርጅት የልማት አጋሮች እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስት በብሔራዊ ምክክር ግጭቶችን በእርቅና ይቅርታ በመቋጨት በዘላቂ ሀገራዊ እርቅና ሰላምን ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ አጋሮችና የአፍሪካ የግል ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ በማቋቋም የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ የማይተካ ሚና ይኖረዋልም ነው ያሉት።
በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ገባይዴ ዶ፤ የትጥቅ ማስፈታትና የመልሶ ማቋቋም የተሀድሶ ስልጠና መጀመሩ የሰላም ስምምነቱ የሰመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ የሚገኘው ጥረትም የጥይት ድምጽን ከማስቀረት ባሻገር የክልሉን ነዋሪዎች ተስፋ የሚያለመልም መሆኑን ገልጸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችም ከተሀድሶ ስልጠናው በኋላ ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ የሰላምና የልማት ምርታማነት አቅም መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘው የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ግዙፍ ቁጥር ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ አስፈላጊ ሂደት ላይ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት በሚያደርጉት ቁርጠኛ አጋርነት ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በምታከናውነው የቀድሞ ታጣቂዎችን የመልሶ ማቋቋም ስራ ድጋፍ ላደረጉ የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ምስጋና አቅርበው በቀጣይም እገዛውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የአውሮፓ ሕብረት እና ለጋሽ ሀገራት ተወካይ ሶፊ ፍሮም-ኢመስበርገር፤ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት በተሀድሶ ስልጠና መልሶ ለማቋቋም የሚደረጉ ድጋፎች የኢትዮጵያን ሰላምና ደኅንነት በጽኑ መሰረት ላይ ለማኖር ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ትርጉም ያለው እርምጃ እየወሰደች መሆኑን የጠቀሱት ተወካዩ፤ ለዚህም የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማትና ለጋሽ አገራት በትብብር እየሰሩ ነው ብለዋል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የፌደራልና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ለወሰዱት ቁርጠኝነት ዕውቅና እንሰጣለን ብለዋል።
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ስልጠና መልሶ በማቋቋም ሰላምና ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዝግጅቱ የታደሙ የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአህጉራዊና ዓለማ አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮችም የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ስልጠና ለመስጠት የተደረጉ የዝግጅት ሂደቶችን የሚያሳየውን ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል።