ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው

ደሴ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ)፡-በደሴ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ2 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የዘመቻ ስራ መጀመሩን አስታወቀ።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ እንደገለጹት፤ በዓይን ሞራ ግርዶሽ የሚሰቃዩ ሰዎችን የህክምና አገልግሎቱን በነፃ በማቅረብ ችግሩን የማቃልል ስራ እየተከናወነ ነው።
የሕክምና አገልግሎቱ ከህዳር 14 እስከ ህዳር 20/2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ በትናንትናው እለት ብቻ 362 ሰዎች ሕክምናውን እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ሕክምናው ከአካባቢው ከተሞችና ዞኖች ከሚመጡ ነዋሪዎች ባሻገር ለአጎራባች ክልል ነዋሪዎች እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ እስካሁን ከአንድ ሺህ 900 የሚበልጡ ታካሚዎችን የመለየት ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።
ዘመቻው በሕክምና መዳን እየቻሉ በተለያየ ምክንያት መታከም ያልቻሉትን ወገኖች ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በሆስፒታሉ የዓይን ሕክምና ክፍል ሃላፊና የዘመቻው አስተባባሪ አቶ እንዳልክ ያረጋል በበኩላቸው፤ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በአብዛኛው ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
"ኪውር ብላይንድነስ ፕሮጀክት" ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር እየተሰጠ ባለው የሕክምና አገልግሎት 6 የዘርፉ ስፔሻሊስት ዶክተሮችን ጨምሮ 30 የዓይን ሐኪሞች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኪውር ብላይንድነስ ፕሮጀክት የአድቮኬሲ ክትትል፣ ቁጥጥርና ግምገማ ማናጀር አቶ አገሩ ከበደ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የዓይን ህክምና የሚሰጡ 25 ሆስፒታሎችን በመደገፍ ዓይነ ስውርነትን ችግር ለመቀነስ እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም ለሆስፒታሎች ግብዓት በማሟላትና ስልጠና በመስጠት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሕክምና በዘመቻ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የዓይን እይታቸው በመዳከሙ ቤት ከዋሉ ሦስት ዓመት እንደሆናቸውና በሆስፒታሉ በተሰጣቸው ህክምና ሙሉ የዓይን ብርሃናቸው መመለሱን የተናገሩት በደሴ ከተማ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትርንጎ አበበ ናቸው፡፡
የአምባሰል ወረዳ ነዋሪ አባ ደመና ኡምነሳ በበኩላቸው፤ በዓይኖቻቸው የማየት አቅም መዳከም በቤት ውስጥ መዋል ተገደው እንደነበረ አስታውሰው፤ በተሰጣቸው ህክምና የዓይናቸው ብርሃን በመመለሱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቦሩ ሜዳ ጠቅላላ ሆስፒታል ባለፉት ዓመታት በተሰጠ የዓይን ሕክምና አገልግሎት ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች አገልግሎቱን መስጠት እንደቻለ ከሆስፒታሉ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።