ቀጥታ፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለሀገር ግንባታ የላቀ ጠቀሜታ እያበረከተ ነው - የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አያን አብዲ  

ጅግጅጋ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ):- የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለሀገር ግንባታ የላቀ ጠቀሜታ እያበረከተ መምጣቱን የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አያን አብዲ ገለጹ።

በክልሉ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል ።

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ አያን አብዲ ለኢዜአ እንደገለጹት "በዓሉ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና መፈቃቀር እንዲጎለብት የላቀ ሚና አለው" ብለዋል። 

በዓሉ መከበር ከጀመረ ወዲህ ለሀገር ግንባታ የላቀ ጠቀሜታ እያበረከተ መምጣቱን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ እየተከተለች ባለችው የፌዴራሊዝም ስርዓት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል የመልማት እድል በማግኘት ዜጎች በአካባቢያቸው ልማት ቀጥታ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያስቻለ  መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮውን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልም በክልል ደረጃ ከህዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በዓሉ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የህዝቡን አንድነትና ወንድማማችነት በሚያጠናክሩ ስራዎች እንደሚከበር አመላክተዋል።

ምክር ቤቱ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ተገቢውን የማስተባበር፣ የመደገፍና የክትትል ስራዎች እያከናወነ መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም