ቀጥታ፡

የአካባቢና ማህበራዊ ተፅእኖ ግምገማ በማድረግ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች ፈቃድ ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች የአካባቢና ማህበራዊ ተፅእኖ ግምገማ በማድረግ ፈቃድ መስጠቱን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሚ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ‘‘ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ‘‘ የአካባቢ ብክለት መግቻ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በሁሉም አካባቢዎች ተከናውኗል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄውን መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ማስጀመራቸውና ለተከታታይ ስድስት ወራት መካሄዱ ይታወሳል።

የንቅናቄው ዓላማ የከተሞችን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን የተከተለ በማድረግ ውብና ምቹ ከተማ መገንባት እንዲሁም የድምጽ ብክለትን መከላከል ነው።

በዚህም ከ6 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሚሆን ህዝብ በአካባቢ ብክለት ተፅእኖ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

በተጨማሪም በባለስልጣኑ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ለሚቀርቡ የፕሮጀክት ጥናቶች የአካባቢ ተፅእኖ ግምገማ መስራትና ማጽደቅ ይገኝበታል ብለዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ለ2 ሺህ 026 የፕሮጀክት ጥናቶች የአካባቢ እና ማህበራዊ ተፅእኖ ግምገማ በማድረግ ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአፈር፣ በውሃ፣ በድምፅ እና በአየር ብክለት ከማህበረሰቡ ሲነሱ ለነበሩ ከ356 በላይ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት መቻሉንም ጠቁመዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ የቆሻሻ መልሶ መጠቀም ልምድን በመገምገም የታዩ ክፍተቶችን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ በ29 የመልሶ መጠቀም ዘርፍ ላይ ለሚሰሩ ተቋማት ድጋፍና ክትትል ተደርጓል።

በዚህም 347 ሺህ 329 ቶን ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ እንደዋለም ጠቅሰዋል።

ኢንቨስትመንት ለሀገር እድገት አስፈላጊ ቢሆንም የአካባቢንና የህብረተሰቡን ሰላም እና ጤንነት በጠበቀ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ አንስተዋል።

ይህንን መሰረት በማድረግም ለተለያዩ ኢንዱስትሪዎች፣ የአበባ እርሻዎች እንዲሁም ሆቴሎች አካባቢን ከመጠበቅ ጋር ተያይዞ የማሻሻያ ስራ እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም