ቀጥታ፡

በባሌ ዞን በመኸር እርሻ በስንዴ ምርት ከተሸፈነው መሬት 14 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 15/2017(ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን በመኸር እርሻ በስንዴ ምርት ከተሸፈነው መሬት 14 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ባለሙያዎች በባሌ ዞን አጋርፋ እና ጋሰራ ወረዳ የስንዴ ምርት ያለበትን ደረጃ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱም በዞኑ የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡ ተገልጿል።

የባሌ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አሊዪ መሐመድ እንዳሉትም፤ በዞኑ 343 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ምርት ተሸፍኗል።


 

ከዚህም 14 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚጠበቅ ጠቁመው የሰብል ሁኔታውም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝናአርሶ አደሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በክላስተር እርሻ ላይ ያለው ግንዛቤ በማደጉ ምርታማነቱ በመጨመር ላይ ነው ብለዋል።

መካናይዜሽንን በመጠቀም ምርታማነቱን እያሳደገ መሆኑን ጠቁመው የምርት ብክነት እንዳይኖር በቴክኖሎጂ የተደገፈ የምርት አሰባሰብ መተግበሩን ገልፀዋል።

በባሌ ዞን የአጋርፋ ወረዳ አርሶ አደር አብዱራህማን መሐመድ፤ ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃር ሁሉንም ዓይነት ግብዓቶች በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በክላስተር በማረስም ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ያነሱት አርሶ አደሩ በሄክታር ከ85 ኩንታል በላይ ምርት በማግኘት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

መንግስት ተረጂነትን ለማስቀረት የወሰደውን ቁርጠኝነት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እያገዙ መሆናቸውን ገልፀዋል።


 

የጋሰራ ወረዳ አርሶ አደር ሂጂ ሙስጠፋ ጀማል ስንዴን በክላስተር በማረስ ከፍተኛ ምርት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የስንዴ ምርት ለገበያ በማቅረብ ሕይወታቸውን መቀየር መቻላቸውን ገልፀዋል።

በመንግሥት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።


 

በጉብኝቱ የተገኙት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ እንደ ሀገር በስንዴ ምርታማነት የተገኘው ድል በሌሎች ዘርፎች ለመድገም እየተሰራ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን ለማስቀረት የወሰደችው እርምጃ ትክክለኛ ለመሆኑ በባሌ ዞን የሚታየው የስንዴ ምርት ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም