ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተላቃ አመርቂ ውጤት እንድታስመዘግብ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተላቃ አመርቂ ውጤት እንድታስመዘግብ አድርጓል
አዲስ አበባ ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተላቃ የዜጎቿን ተጠቃሚነትና ብሔራዊ ፍላጎቶቿን በማረጋገጥ ረገድ አመርቂ ውጤት እንድታስመዘግብ ማድረጉን ገለጸ።
የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በፌዴራል ተቋማት ደረጃ የተከበረ ሲሆን "የኃሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ኃሳብ የፓናል ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
ከፖናል ተወያዮቹ መካከል የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ተቋማት የብልፅግና ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲ እንዲወለድ ምክንያት የሆነው ከለውጡ በፊት የነበሩ ስብራቶች ናቸው ብለዋል።
በለውጥ ሂደት የተፀነሰና ለውጡን የመራ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።
ለውጡ የፖለቲካ ምህዳር የሰፋበት፣ የሚዲያ ነፃነት የተረጋገጠበት፣ የሕግ ማሻሻያና የተቋማት ሪፎርሞች የተደረጉበትና የዲሞክራሲ ምህዳር የሰፋበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ብልፅግና አካታችና አሰባሳቢ ሆኖ የመሀል ፖለቲካ መንገድን በመከተል የትርክ መዛባት እንዲስተካከል መሰረት የተጣለበት እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል የትርክት ግንባታ ሂድት የተጀመረበት፣ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትና የሽግግር ፍትህ ሂደት የተጀመረበት እንደሆነም እንዲሁ።
በጥቅሉ ለውጡ አገርን ከመስቀለኛ መንገድ ያሻገረ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰላም ማረጋገጥ፣ አሰባሳቢ ትርክት ግንባታን ማጠናከርና የፖለቲካ ምህዳር የማስፋት ስራዎችን በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።
የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ለውጡ ከማክሮ ኢኮኖሚ የፋይናንስ ቀውስ ሀገርን የታደገ እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
የ10 ዓመት የኢኮኖሚ መርኃ ግብር የተቀረፀበትና የዕዳ ሥጋቶች የተቃለሉበት፣ የዋጋ ንረት መቆጣጠር የተቻለበት እና ኢንቨስትመንት የተስፋፋበት እንደሆነ አብራርተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ዘመን የብዝሃ ኢኮኖሚ ስርአት ላይ ትኩረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ ኢኮኖሚውን ዘላቂና ተወዳዳሪ ለማድረግ አይተኬ ሚና እንደተጫወተም እንዳሁ።
የፖለቲካ ኢኮኖሚው በቀጣናው ግዙፍ መሆኑን ገልፀው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ለዕድገት ምቹ የሆነ፤ የዕዳ ጫና ያቀለለ፣ ዕድገቱም ዘርፈ ብዙ የሆነ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ያሻሻለ ነበር ብለዋል።
በጥቅሉ ኢኮኖሚው ዘመናዊና ተወዳዳሪ ሆኖ የሚቀጥል ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ገልፀው፤ ዘላቂ አሳታፊና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት የሁሉንም አካላት ትብብር ይጠይቃል ነው ያሉት።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በማህበራዊ መስኮች የተመዘገቡ ድሎችና ስኬቶችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ የማህበራዊ ልማት አካታችነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልፀዋል።
ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ለማረጋገጥ በድህነት ቅነሳ፣ በጤና ልማትና በትውልድ ግንባታ ትልልቅ ድሎች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ጥራትና አካታችነት መሰረትያደረገ የትምህርት ስርዓት መገንባቱን ጠቅሰዋል።
ከጤና ስርዓት አኳያ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ዘርፉ ዘመኑን እንዲዋጅ በመደረጉ መከላከል ብቻ ሳይሆን አክሞ ማዳን መቻሉን፣ የእናቶች ጤናና ሕይወት ያሻሻለ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን፣ ብዝሀነትን ማዕከል ያደረጉ የባህል ልማት ስራዎች መከናወናቸውን በማንሳት ሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚ ያደረጉ ድሎችን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በመሰረተ ልማት ስራዎችም በአረንጓዴ ፓርኮች እና በኮሪደር ልማት ስራዎች አካታችና ፍትሀዊነትን በማረጋገጥ ማህበራዊ ልማት መሰረት ያደረጉ ስለመሆናቸወም ጠቅሰዋል።
የተፈጠረው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች እያስገኘ በመሆኑ አጓጊ ጅምሮችን ከዳር ለማድረስ የሁላችንንም ቅንጅት ይጠይቃል ብለዋል።
'የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ስኬቶችን አብራርተዋል።
የውጭ ግንኙነት ስራዎች በብልፅግና ዘመን ሀገራዊ ክብርና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የዜጎችን ክብር ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
በቀጣናዊ ትብብር፣ በሰላምና ደህንነት ስራዎች ረገድ በ5 ዓመታት አኩሪና የኢትዮጵያን ከፍታ ያረጋገጡ የውጭ ግንኙነት ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጥ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መተግበሩን ገልፀው፤ ደፋር እና በብሔራዊ ጥቅም ላይ የማይደራደር የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እየተከተልን ነው ብለዋል።
ከሁኔታዎች ጋር የሚራመድና ለብሔራዊ ጥቅም የወገነ ዲፕሎማሲ መተግበሩን በመጥቀስ፣ የምዕራብም የምስራቅም ጎራ የወገነ ሳይሆን ጥቅምን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።