ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ይደረጋል - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አሶሳ፤ ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ድርጅት የስራ ሃላፊዎች "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን አስመልክቶ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አስተባባሪ አያና ዘውዴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢንዱስትሪውን የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚያስችል ቁመና ላይ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።


 

ለኢንዱስትሪዎች መጠናከር የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር እና ቅንጅታዊ አሰራር ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ በክልሉ ያሉትን ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ለማስገባት አስፈላጊውን ዕገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዜጎች የአገር ውስጥ ምርት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር)፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዜጎች የአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።


 

ንቅናቄው በኢንዱስትሪዎች ላይ የሚታየውን ችግር ለማቃለል እና በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት ለመቀየር ብዙ ስራ ይጠበቃል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የተፈጥሮ ማዕድናትን እና የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተደድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ንቅናቄውን እስከ ታችኛው መዋቅር በማውረድ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብም እንሰራለን ብለዋል።

በክልሉ 56 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች እንዳሉም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም